ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
በኢትዮሚዲያ ላይ በለንደን ላይ ያደረጉትን ንግግር ከዚህ በታች የተቀነጨበውን አየውና ይህንን ልፅፍ ተነሳሳሁ። “የኦሮሞ ወጣቶችን ወክዬ ለውጭው ማህረሰብ የማስተላልፈው መልዕክት አለኝ። ካሁን በዋላ በኢትዮጵያ ቢሆን ቢሆን ታግለን መብታችንን አስመልሰን ከሌሎች ጋር አብረን እንኖራለን። ካልሆነ ግን ያችን ሀገር በታትነን ጥለናት እንሄዳለን እንጂ እንደ ትላንቱ የማይረቡት እላያችን ላይ ተጭነው እንዲያስተዳድሩን አንፈቅድም።” - ጀዋር መሐመድ፥ ከለንደን ንግግር ከኢትዮሚዲያ የተወሰደ። በመጀመሪያ አሳቤን ይረዱልኝ። በክርክር ለማሸነፍ አሳቡም ምኞቱም የለኝም። እርስዎንም እንደ ጠላት ለመቁጠርና ለመፈረጅ በልቤ ውስጥ ያለው ፍቅር አይፈቅድልኝም። ነገሬ ከአስተሳሰብዎ ጋር ነው። ለማሳመን ብዙ ትንታኔ አልገባም። ቃሌን አጭር በማድረግ ከቃሌ ጀርባ ያለውን ቅን መንፈስ እንዲረዱ ተስፋ ማድረግን እመርጣለሁ። እርስዎ እስላም እኔ ክርስቲያን፥ እርስዎ ኦሮሞ እኔ አማራ መሆናችን ለመግባባት እንቅፋት ይሆናል ብዬ አላስብም። ለእኔ እርስዎ የሀገር ልጅ ነዎት። ሃይማኖት የግል ሀገር የጋራ ነው የሚለውን አባባል ልቀያይረውና፥ በጥንድ እውነት መግለፅ ይፈቀድልኝ፤ ሃይማኖት የግል ፈጣሪ የጋራ ነው። ዘራችን የግል ኢትዮጵያ የጋራ ናት። ስለዚህም የጋራ በሆነ ነገር ላይ ሁለታችንም አንድ ነን። በዚህ መንፈስ እንዲያደምጡኝ አደራ እላለው። በመጀመሪያ ራሴን ላስተዋውቅና፥ እኔ ያለፈውን የታሪክ ቁርሾ በይቅርታ ዘግተን፥ የወደፊቱን ታሪካችንን በፍትህ መስርተን፥ ነፃ የሚያወጣንን እውነት ተነጋግረን፥ አዲሲቷን ኢትዮጵያ እንገንባ ብዬ የምሞግት ነኝ። ይህንን ካልኩ አሁን ወደ ዝርዝር ሀሳቤ ልግባ። የጎንደር ሕዝብ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ወንድምነት በአደባባይ አጋርነቱንና ፍቅሩን ሲያስተጋባ፥ የፍቅር ቋንቋ መናገሩን ያሳይ ነበር። ያንንም የፍቅር ጥሪ ወንድሙ የኦሮሞ ሕዝብ ተረድቶ፥ ምላሹን ፍቅሩንና አጋርነቱን በአደባባይ ሲያሳይ ፍቅርን መናገሩ እንደሆነ ይገልጥ ነበር። ይህንን የሕዝብ ፍቅር ቋንቋ ለምድራችን ፈውስ ተስፋ ጭላንጭል ያመጣል ተብሎ ሲጠበቅ፥ በዚህ ወሳኝ ወቅት በለንደን ያቀረቡት ንግግርዎ ተስፋውን በዜሮ እንዳባዙት ይቆጠራል። ይህንን ግልፅ ደብዳቤ ለመፃፍ የፈለኩት እንኪያ ሰላምታ ከእርስዎ ጋር ለመግጠም ሳይሆን፥ ለሚያየንና ለሚሰማን ሁሉ መግባባትን ፍንጥቅ ማድረግ ይቻል ይሆናል የሚል ተስፋ ፍቅር በልቤ ውስጥ ስለጫረብኝ ነው። ለዚህም የምተማመነው በሀገር ልጅነታችን ላይ ያለኝ አመኔታ ነው። ኢትዮጵያ የአንድነቷ መሰረት የሕዝቧ ማንነት ነው። የኢትዮጵያ አንድነት በመንግስት ስራ ወይንም መንግስት በሚያወጣው አዋጅ ቁጥጥር ስርም አይደለም። ነገሩን ካስተዋልነው በሊሂቃን አስተሳሰብና ፍልስፍና ስርም አይደለም። በእኔና በእርስዎ እጅም አይደለም። የታሪክ ጉዳይ ሆኖ የኢትዮጵያ አንድነት ጅማሬው ላይ የመንግስታት እጅ ቢኖርበትም፥ ሕዝቡን የሚያስተሳስረው ፍቅር ግን ሰው ሰራሽ አርተፊሻል ሳይሆን “ተፈጥሯዊነት”(organic) ነው። ይህን ሕዝቡ በታሪክ አጋጣሚና በፈጣሪ አሳብ አብሮ ለዘመናት በመኖር ያመጣው እውነታ ነው። ኦሮሞ ፍታዊ ሆኖ የሚኖርበት ለመድረስ በመንገዱ ላይ የቆመው ኢትዮጵያ ሳትሆን እንደ እርስዎ ያለው አስተሳሰብ ነው ብዬ እገምታለሁ። ለኔ ኢትዮጵያ ከኦሮሞ ተነጥሎ በኦሮሞ የድል መንገድ ላይ የቆመ ደንቃራ አድርጌ አልወስድም። ለምን ቢባል መላውን ኢትዮጵያ በጂኦግራፊ፥ በቤተሰብነት፥ በአብሮ ነዋሪነት፥ በደግነቱ አያይዞ፥ ተጋብቶ ተደባልቆና ተዋልዶ እዚህ ያደረሰው በተቀዳሚነት የኦሮሞ ሕዝብ ነው። ፍትህና ዲሞክራሲ ያለባት መድረሻ እንድትሆን የሚፈልጉት ኢትዮጵያ ከሆነ መነሻዎን ኢትዮጵያ ማድረግ ያለብዎት ይመስለኛል። ያልተነሱበትን ነገር መድረሻ ላይ አገኘዋለው ማለት ዘበት ነው። ለእኔ ኦሮሞ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩሕ ተስፋ ለመቅረፅ የመሪነቱን ሚና ይጫወታል። ለዚያም በሀገር ቤት ያለው የኦሮሞ ሕዝብ የመሪነቱን ሃላፊነት በብቃት እየተወጣው ነው። እርስዎስ አጥር ሆኖ ከሌላው ሕዝብ የሚከልልዎትን የውልጃ ማንነት ሳይለቁ(ወደው አይደለም ኦሮሞ ሆነው የተወለዱት)፥ በምርጫዎ ከሁሉ ሕዝብ ጋር በእኩልነት የሚያያይዝዎትን ኢትዮጵያዊነትን መርጠው በጋርዮሽ ቢሞግቱ ምን ይመስልዎታል? አንደኛ ኦሮሞ መሆንዎን መምረጥዎ ባልከፋ፥ መልካም ነውና። ለነገሩ ሁሉም በግሉ በመጀመሪያ የተለያየ ዘር ግኝት ነው። ታዲያ የሚያስተሳስረን ጉራጌው ጉራጌ ኢትዮጵያዊትን አንግቦ፥ ጋምቤላው ጋምቤላ ኢትዮጵያዊነትን ወዶ፥ ትግሬው ትግሬ ኢትዮጵያዊነትን መርጦ፥ አማራው አማራ ኢትዮጵያዊነትን ተቀብሎ ወዘተረፈ በጋሪዮሽ መያያዛችን ነው። ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ መሆንና ለኦሮሞ እኩልነት ማቀንቀን የሚቃረኑ አይደሉም፥ እንደውም የሚደጋገፉ እንጂ። ዋነኛው ጉዳይ ከኖርንም አብረን፥ ተበታትነን ከጠፋንም አብረን እንደሆነ በማወቅ የመቆራኘታችንን ሚስጢር ጥልቀቱን ማስተዋሉ ላይ ነው። ኢትዮጵያን በታትኖ ኦሮሞን መገንባት የሚለው አሳብ የማይሆን ነገር ነው። በኢትዮጵያ መቃብር ላይ የሚገነባ የኦሮሞ በረከት በዚያች ምድር ይኖራል ብሎ ማሰብ ከንቱ አስተሳሰብ ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መቃብር ካለ፥ ከኢትዮጵያ መቃብር ስር የኦሮሞ መቃብር አለ። ለምን ቢባል ከማንም ይልቅ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የሚያሰኛትና እንደ ደም ስር ሁሉንም የሚያያይዘው ኦሮሞ ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመዋለድና በመደባለቅ ስርና መሰረት ስለሆነ ነው። ነገር በምሳሌ እንዲሉ ሁላችንም ያለነው ውቂያኖስ ላይ የሚንሳፈፍ ኢትዮጵያ በሚባል ትልቅ መርከብ ላይ ነው። እርስዎ የሚሉት ቢሆን ቢሆን ተባብረን መርከቡን በእኩልነት እየኖርንበት እንሂድ፥ ካልሆነ መርከቡን በታትነን በኦሮሞ ጀልባ እንኖራለን ነው። ያስተውሉ፥ 1ኛ/ ሌላው ይበታተን የሚሉት ትልቁን 80 በላይ ብሔረሰብ የሚይዘውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ነው። 2ኛ/ ኦሮሞ እንደ ጀልባ በኢትዮጵያ መርከብ ላይ የተቀመጠ ማንነት ያለው አይደለም። ኦሮሞ የመርከቡ አካልና መካከለኛ ክፍል ነው። ይህ መሬት ላይ ያለ በሕዝቡ አብሮነት ለዘመናት የተገለጠ ሐቅ ነው። 3ኛ/ መርከቡ ከተበታተነ፥ የመርከቡ መካከለኛም አብሮ ሰምጦ ይቀራል። ከዚህ ውጭ ያለ አስተሳሰብ ሕልውና በሕልም ደረጃ ያለ ነው። 4ኛ/ የመርከቡን መሪ ማን ይያዝ የሚለው ጉዳይ የእኛ ምርጫ አይደለም። የእኛ ትግል መሪዉን ለመያዝ ሳይሆን፥ መሪዉን የሚይዘውን አካል ሕዝብ እንዲመርጥ እውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲኖር ነው። እውነተኛ ዲሞክራሲ ባለበት ብዙ የሕዝብ ቁጥር ያለው ኦሮሞ ከሁሉ ይበልጥ ይመቸዋል። ታዲያ የነገሬ ፍፃሜ ይህ ነው፥ ከ 50 ዓመታት በላይ ከቆየው የኦሮሞ ትግል ልምድ ከቀሰሙ በዋላ የደረሱበት ይህ አስተሳሰብዎ፥ ሁሉም የሚፈልገውን ይህንን ዲሞክራሲ እውን ለማድረግ የሚያስችል መላ በውኑ ነውን? ለማንኛውም ለሁላችንም ልቦና ይስጠን። አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ!
0 Comments
Leave a Reply. |
Details
MemberZelalem Eshete, Ph.D.
Deeper Walk With God Book on Ethiopia
This book makes a case for a paradigm shift in our thinking on the matter of Ethiopia. Instead of feeling powerless in our usual political saga, ethnic divide, and religious tensions, the book motivates us to look deeper, rediscover our true identity, and arise to make change. The greater power of change is with the people. The world has heard enough of our suffering. Let's spotlight the other face of Ethiopia: To Be Known As We Truly Are.
The world has heard enough of our lack of civilization. Let's spotlight the other face of Ethiopia: We Are One Big Intelligent Family. The world has heard enough of our poverty. Let's spotlight the other face of Ethiopia: Going Global Together. |