EthioFamily.com

  • EFF

10/3/2016

አራቱ የኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳዎች 

0 Comments

Read Now
 

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
 
ዛሬ ኢትዮጵያ አስከፊ ችግር ውስጥ ወድቃለች። ነገር እየተባባሰና የሰው ሕይወት እየተቀጠፈ ባለበት በዚህ ወቅት፥ ኢትዮጵያ ልጆቿ አደጋ ላይ ሳይወድቁ ይህን ክፉ ጊዜ የምታልፍበት መውጫ ቀዳዳ ያጣች ትመስላለች። መውጫ ቀዳዳዎች ከአንድም አራት አሉላት ይባል ይሆናል። መውጣትም አይቀሬ ነው። ሁሉም ነገር ያልፋልና። ግን ዋናው ጉዳይ በአንደኛው መውጫ ቀዳዳ እንደምንም ብሎ መውጣቱ አይደለም። ይልቁንስ ልጆቿ ኖረውላት፥ ፍቅርን አትረፈውላት፥ ታሪክን ሰርተውላት፥ በዓለም አንገቷን ቀና እንድታደርግ አድርገውላት፥ በድልና በክብር ካለችበት አደጋ የሚያስፈተልካት መውጫ ቀዳዳው የትኛው እንደሆነ ለይቶ ማወቁና መተግበሩ ላይ ነው።
 
ታዲያ ለዚህ ፈውስን በሚያመጣው መውጫ ቀዳዳ በኩል ኢትዮጵያን የሚያስመልጥ ጅግናዎች ያስፈልጉናል። ለመሆኑ ታዲያ ኢትዮጵያ የጀግና አገር ናትን? መልሱ አንድ ሳይሆን ሁለት ነው፤ ያውም ተቃራኒ የሆኑት አዎ እና አይ ናቸው። እንግዲህ የዚህን ጭብጥ ለመረዳት ወደ ዝርዝሩ እንለፍ።
 
ጠ/ሚኒስቴር ሃይለማርያም “እርምጃ እንዲወሰድ!” እያሉ ሲናገሩ ይደመጣሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚዎች ሽምግልና ቦታ የለውምና “አትደራደር!” እያሉ ሲጮሁ ይሰማል። በዚህ መሃል ሽምግልና ቦታ ይሰጠው ብለን የምናቀነቅን ሰዎች ሁለቱም ወገን እንዲሰማን ስንሟገት እንገኛለን። በዚህ ግርግር ቆም ብለን፥ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ምኞትና ፍላጎት ምን ይሆን?” ብለን እንድንጠይቅ ግድ ሊለን ይገባል።
 
ሽምግልና መፈለግ የደካማነት ምልክት ሳይሆን የእውነተኛ ጀግንነትን ጥበብ የሚያመላክት ነው። ምክንያቱም ማሸነፍን ብቻ ሳይሆን ከማሸነፍ በስቲያም ማሸነፍን ያረጋግጣልና። ይህ መንገድ ቀጭንና ጠባቧ መንገድ ናት። እንደሚታወቀው ሁለት አይነት የሽምግልና አካሄድ አለ። አንድም አድሏዊ የሆነ ከሃይለኛው ጋር የወገነ የይስሙላ ሽምግልና ሲሆን፥ ሌላኛው ደግሞ አድሏዊ ያልሆነ ከማንም ያልወገነና እውነተኛ ሽምግልና ነው። በዚህ ፅሁፍ ላይ የምናየው ሽምግልና ፋይዳ የማይሰጠውን የይስሙላ ሽምግልና ሳይሆን፥ ኢትዮጵያን ካለችበት አጣብቂኝ እንድትወጣ ድልድይ የሚሰራውን እውነተኛውን ሽምግልና ነው። የዚህ እውነተኛ ሽምግልና ግብና ዓላማ በውይይትና በመግባባት አገሪቱን በሰላማዊ መንገድ ወደ ዘላቂ ዲሞክራሲ ፍትህ እኩልነትና ዕድገት የሚያመራውን ሂደት ለመፍጠር ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው።
 
ሽምግልናን በተመለከተ መንግስት ሁለት ምርጫ አለው። አንድም በመግባባት መንገድ መሄድ አለበለዚያ በእንቢተኝነት ዘራፍ ብሎ  “ደምስሰው!” እያለ መገስገስ። አማራጭ ሃይሎችም ሁለት ምርጫ አላቸው። አንድም በመግባባት መንገድ መሄድ አለበለዚያ ዘራፍ ብሎ “ገርስሰው!” እያሉ መጓዝ። መንግስትና ተቃዋሚ የሚመርጡት ምርጫዎች ኢትዮጵያን ከአራቱ አንዱን አካሄድ እንድትሄድ ያደርጋታል። እያንዳንዳቸውን በየተራ ለመመልከት እንድንችል እነዚሁ አራቱ የኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳዎች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።
 
(1) ተቃዋሚ ሽምግልናን ፈልጎ መንግስት ግን ሽምግልናን ባይፈልግ፥
(2) መንግስት ሽምግልናን ፈልጎ ተቃዋሚ ግን ሽምግልናን ባይፈልግ፥
(3) ሁለቱም ወገን ሽምግልናን ባይፈልግ፥
(4) ሁለቱም ወገን ሽምግልናን ቢፈልግ።
 
አንደኛው የኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳ፥  
መንግስት ሽምግልናን ባይፈልግና ተቃዋሚዎች ሽምግልናን ቢመርጡስ
 
አንድም ዘርፈ ብዙ የሆኑትን አማራጭ ሃይሎችን መግባባት እርስ በርስ ያቀራርባቸዋል። አንድ ድምፅ ይሰጣቸዋል። ልዩነታቸውን እንዲያጠቡ ያበረታታቸዋል። አንድነት ሃይል ይሆንላቸዋል። ጥያቄው ሕዝብ ያሸንፋል ወይ? አይደለም። ሕዝብ ሁልጊዜ አሸናፊ ነው። ግን እንዴት ያሸንፋል? ነው ጥያቄው። መግባባትን ለመረጠ አማራጭ ሃይል፥ ሕዝብ ስልጣኑን ቢሰጠው የሕዝብ መንግስት ለመሆኑ የተረጋገጠ ይሆናል። ቁምነገሩ እዚህ ላይ ነው። ከማሸነፍ ባሻገር ማሸነፍ አለ የሚባለውም ለዚህ ነው። ከማሸነፍ ባሻገር ያለው ማሸነፍ ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ማየት ነው። ይህም ይቻላል። ኢትዮጵያ መከራ ይበቃታል። እርስዋ እየደማች ተራ በተራ ንጉሶች የሚፈራረቁባት ጊዜ ያክትም። ልባችንን መጣል ያለብን ኢትዮጵያ ታሸንፍ ዘንድ ነው። ስለዚህም ነው ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ እንዳይሆን መግባባትን ዛሬውኑ ጓደኛ ማድረግ የሚበጀው። 
 
ደግሞም አማራጭ ሃይሎች መግባባትን እድል ቢሰጡትና መንግስት እንቢ ብሎ ሃይሉን ብቻ ማፈርጠም ቢቀጥል፥ ይህ አካሄድ መግባባትን እንቢ ያለውን መንግስት ብቻውን እንዲቀር ያደርገዋል። ሕዝብን ሁሉ አንድ ወገን አንድርጎ፥ እምቢተኛውን መንግስት ያጋልጠዋል። እንቢተኝነቱ እርሱን የሚደግፉት ሁሉ እንዲክዱት ያደርጋል። ይህን አደጋ ለማምለጥ ምንም መላ አያገኝም። ሌላውን አጥፍቶ ሳይሆን እንዲሁ ብቻውን ራሱ እራሱን አጥፍቶ ታሪክ አልባ ሆኖ ስፍራውን ይለቃል።
 
ሁለተኛው የኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳ፥
መንግስት ሽምግልና ቢፈልግና ተቃዋሚዎች ለሽምግልና ቦታ ባይሰጡትስ
 
መንግስት መግባባትን በስራ ላይ ለማዋል መድረኩ በእጁ ነው። እንደሚገባ ሃላፊነቱን በዚህ ረገድ መወጣት የመሪነቱ ግዴታ ነው። ጊዜ በወሰደ መጠን እድሉ ከእጁ እያፈተለከ እንደሆነና ኢትዮጵያን አደጋ ላይ እየጣላት እንደሆነ ማወቅ አለበት። ነገር ግን ነገ ሳይል ዛሬ ሽምግልናን ቢቀበል ታሪክ ሰሪ መንግስት ሆኖ በታሪክ መዝገብ ሊታወስና አዲስ ጅማሬን ለኢትዮጵያ የማውረስ አጋጣሚ አለው። መንግስት መግባባትን ሲመርጥ፥ ለሚያልፍ ጊዜ ስልጣን ላይ መቆየት ላይ ያነጣጠረ ራዕይ ሳይሆን፥ ራዕዩን አስፍቶ ፈር ቀዳጅ ድርጊትን አድርጎና ለታሪክ የሚቀር አሻራ ትቶ እንዲያልፍ ያሳስበዋል። ሕዝብ ብሎ በስልጣን ቢቆይም በክብር፥ ሕዝብ ብሎ ስልጣን ቢለቅም በክብር ይሆንለታል። ላስተዋለው እንዲህ ያለ ታሪክ ሰሪነትን በጀማሪነት የሚታደል አንዱ ጀማሪ ብቻ ነው። ይህንን ዕፁብ ድንቅ የሆነውን እድል የሚቀናጀው የመግባባትን ጥሪ በእውነት ሲቀበል ነው።
 
በሌላ በኩል መንግስት የመግባባትን ሰላማዊ ጥሪ ለሁሉም ቢያቀርብና ተቃዋሚዎች ለሰላሙ ጉዞ ስፍራና ቦታ ካልሰጡ፥ ጉዳያቸው ስለ ኢትዮጵያ ሳይሆን መንግስትን አውርዶ እራስን ዙፋኑ ላይ የማስቀመጥ ሩጫ መሆኑ ይታወቅባቸዋል። ተሳክቶላቸው እንኳን መንግስት ቢለቅ፥ መግባባትን ንቆ በዘራፍ ቤተ መንግስት የደረሰ አማራጭ ሃይል ሁሉ አንድነትን ፈጥሮ ለመጓዝ ያስቸግረዋል። ባሳለፍነው ታሪክም ያየነው እንደማይቻል ነው። በመግባባት የዛሬውን ልዩነት ዛሬ መፍታት እንቢ ብሎ ለይደር ያስቀመጠ፥ ያኔ ስልጣኑ ተይዞ ልቡ ከየት ይመጣል? ያው አንዱ እንደተለመደው ደግሞ ስልጣኑን ይይዝና “ምድጃ ቢለዋውጡ ወጥ አያጣፍጥም” እንዲሉ ለኢትዮጵያ ጠብ የሚል ምንም ነገር ላይፈጠር ይችላል። እንዲያውም ከድጥ ወደ ማጡ እንዲባል የባሰ ቢመጣ ምን የሚያስገርም ነገር አለ?
 
ሶስተኛው የኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳ፥
ሁለቱም ወገን ሽምግልናን ዓይን ላፈር ብለው በዘራፍ ጎዳና መንጎድ
 
ለዚህ ምንም ማብራሪያ መስጠት አያስፈልገውም። ሁሌም ለዘመናት ያየነው ታሪካችን ነው። ለውጭ ጠላት ያሳየነው “እውነተኛ ጀግንነት” ብዬ ስጠራ፥ ለእርስ በርስ ባለብን ግጭት አፈታት ላይ ይሳየነው ዘራፍነት “የክስረት ጀግንነት” ብዬ እፈርጃለው። ምክንያቱም በውጭ ጠላት ላይ ያሳየነው ዘራፍነት ኢትዮጵያ አሸንፋለችና እውነተኛ ጀግንነት ነው። በሌላ መልኩ እርስ በርስ ባለን ግጭት ላይ ያሳየነው ዘራፍነት ኢትዮጵያ ከስራለችና የክስረት ጀግንነት ነው። ኢትዮጵያ በምን ከሰረች ቢባል፥ ዲሞክራሲና እኩልነት ለሕዝቡ ያላስገኘ ድርጊት ስለ ነበረ ነው። ለዚህም ነው እርስ በርስ ባለው የውስጥ ችግር ኢትዮጵያ እውነተኛ ጀግንነትን ለማየት እስካሁን አልታደለችም ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ የሚቻለው።
 
አራተኛው የኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳ፥  
ሁለቱም ወገን ሽምግልና ቢፈልጉ
 
ጉዳዩ በእውነት ስለ ኢትዮጵያ እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ይታያል። ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ መሪዎች ከራሳቸው የስልጣን ጥማት ይልቅ የሕዝቡን የልብ ትርታ አደመጡ ይባላል። ቁምነገሩ መንግስትን በስልጣን ማቆየት ሳይሆን፥ ወይም ደግሞ መንግስትን ከስልጣን ማውረድ ሳይሆን፥ የሕዝብ መሻት እንዲሆን ሁለቱም ወገኖት ራሳቸውን ለሰላም መንገድ መስዋዕት አድርገው ሊሰጡ መወሰናቸው ነው።
 
ሁለቱም ወገኖች፥ በስልጣን ላይ ያለውም ሆነ፥ ወደ ስልጣን ልምጣ ባዩ ቁጭ ብለው የሚደራደሩት ስለ የራሳቸው የስልጣን እጣና ፈንታ ሳይሆን፥ ስለ ሕዝብ ስንል ምን እናድርግ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ነው። የመደራደሩ ውጤት የሕዝብን የበላይነት ለማረጋገጥ ነው። ይህ ነው እውነተኛ ጀግንነትን የሚጠይቀው። ይህ ነው ጥበበኛ የሚያሰኘው። ይህ መንገድ ነው እስካሁን በኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ውስጥ ያልታየው።
 
ኢሜል አድራሻ፡ ethioFamily@outlook.com
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

Share

0 Comments



Leave a Reply.

Details

    Member

    Zelalem Eshete, Ph.D.
    Deeper Walk With God
    Picture
    Book on Ethiopia
    This book makes a case for a paradigm shift in our thinking on the matter of Ethiopia. Instead of feeling powerless in our usual political saga, ethnic divide, and religious tensions, the book motivates us to look deeper, rediscover our true identity, and arise to make change. The greater power of change is with the people.
    The world has heard enough of our suffering. Let's spotlight the other face of Ethiopia: To Be Known As We Truly Are.

    The world has heard enough of our lack of civilization. Let's spotlight the other face of Ethiopia: We Are One Big Intelligent Family.

    The world has heard enough of our poverty. Let's spotlight the other face of Ethiopia: Going Global Together.

    RSS Feed

  • EFF