ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
ሕዝብ ተነሳ። ይህ ከወትሮው የተለየ አነሳስ ይመስላል። ከአንዴም ሁለት ጊዜ ይህ ሕዝብ ተነስቶ ሲያበቃ እድሉን ለልጆቹ በአደራነት ሰጥቶ ሲቀመጥ፥ መሪዎቻችን የስልጣን ርክክብ አካሄደው ሕዝቡን በዜሮ እየሰደዱት ስልችቶታል። ቁጭ ብድግ ማለቱ በቃኝ ያለ ይመስላል። አሁን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መነሳቱ፥ የስልጣን ርክክብ ለማካሄድ ሳይሆን፥ ዳግም እንደገና መነሳት በማያስፈልገው ሁኔታ ስልጣኑን ራሱ ወስዶ ተረጋግቶ ለመቀመጥ ነው። ቀድሞ ነገር ባለጉዳዩ ሕዝብ ቁጭ ብሎ መሪዎቻችን ሲተራመሱና ሕዝቡን ራሱን ሲያተራምሱት ምንም ያለማድረጉ በውጭ ለተመልካች ሲታይ ምንም እንደማያውቅ ያስመስለው ይሆናል። እውነቱን ብንመረምር ግን የምናስተውለው ሁሉን አዋቂ እንደሆነና፥ ዝም ያሰኘው ትዕግስቱ መሆኑ በገባን ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲታገስ መሬት ነው። ይሸከማል፥ ይችላል። ረዥም ጊዜ ይሰጣል። ፅዋ ሲሞላና ጊዜው ሲደርስ ይህ ሕዝብ ጠያቂ ነው። በውጭ ሲታይ ሕዝቡ ጉዳይ ፈፅሙልኝ ብሎ አቤቱታ የሚያቀርብ ይመስላል። ግን አሁን እንደዚያ አይደለም። ቀረብ ብለን፥ አጥልቀን ብናይ ይህ ህዝብ በመልካም አስተዳድሩኝ እያለ መንግስትን እየተማፀነ አይደለም። ደግሞም ስም ጠርቶ እከሌ ይግዛኝ ብሎም እየተሟገተ አይደለም። ሕዝቡ እያለ ያለው ስልጣን የሕዝብ ነውና ለሕዝቡ የስልጣን ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥ ድምፁ እንዲሰማ ነው። መንግስት የሕዝብ ጥያቄ መልስ እሰጣለው ብሎ ጥልቅ ተሃድሶ ላካሂድ ብሎ ተነስቷል። ተቃዋሚ የሕዝብ ጥያቄ እመልሳለው ብሎ ሕገ መንግስት ለማርቀቅ ተነስቷል። በፊት ለፊት የማይታየውን እውነት ለማየት ብንጥር ግን ሕዝብ እያለ ያለው፥ ጊዜው የሁለቱም ተፎካካሪዎች የመምራት ጉዳይ ሳይሆን ሕዝቡ ራሱ የሚመራበት ወቅት መሆኑ ነው። ጊዜው መሪዎቻችን ስፍራቸውን ለሕዝቡ ምሪት የሚለቁበት እንጂ በየፊናቸው በነፍስ ወከፍ ለመምራት ሽር ጉድ የሚሉበት ጊዜ አይደለም። ይልቁንስ ሕዝብ መሪዎቹን ለመምረጥ የስልጣን ባለቤት ሆኖ፥ ድምፁ የሚሰማበትና የሚከበርበትን መድረክ ለማመቻቸት እንወያይና እንግባባ። መንግስትም ሰምቶ ይታዘዝ፥ ተቃዋሚም ሰምቶ ይቀናጅ። የሕዝቡ ቆራጥነት የትዕግስቱ ውጤት ነው። ጊዜው እስኪደርስ ትዕግስቱ ሲገርም፥ ጊዜው ሲደርስ ደግሞ ቁርጠኝነቱ የሚደንቅ ነው። ውሎ እንዲያድር ፋታ አይሰጥም። በውጭ ሲታይ ለብዙ ጊዜ የታየው ትዕግስቱ አሁንም አለ ብለን እንታለል ይሆናል። ሕዝቡ ከዝምታውና ከመቀመጫው ሲነሳ ቶሎ ብሎ መታዘዝ ማስተዋል ነው። የለመደች ጦጣ ሁልጊዜ ሽምጠጣ ብለን እንደለመድነው እንቀጥል ብንል፥ መሬት የሆነው ሕዝብ እሳት ሆኖ ይበላናል። ስልጣኑን የያዘው የሙጥኝ ማለቱን ትቶ፥ ተቃዋሚዉም ስልጣኑን መቋመጡን ትቶ፥ ሕዝቡ ልምራ ሲል በእሽታ ሁሉም የየግል ምኞቱን ለቆ ይመራ። ለዚህም ዓላማ ይህ ሕዝብ በእውነት የስልጣኑ እውነተኛ ባለቤት የሚሆንበትን መፍትኤ በአስቸኳይ ይመከርበት። አሁን ልተርክ የተነሳሁት ፊት ለፊት ያለውንና ሁላችንም ያሰለቸንን፥ ግን እውነት ስለሆነው ታሪካችንና ተጨባጭ ሁኔታዎቻችን አይደለም። ደግሞም እውነቱ አድክሞኝ የሌለ ነገር ፈጥሬ አፈታሪክ ለማውራትም አይደለም። ዓላማዬ ፊት ለፊት ከሚታየው እውነት ጀርባ ያለውን ግዙፉን የማይታየውን እውነት አስተውለን፥ የሚገርመውን ነገር እንድናውቅ ነው። እንዴት ማለት ጥሩ ነው። እንግዲህ ከስር መሰረቱ እንጀምር። 1ኛ/ ሕዝቡ የሚገርም ነው። የሕዝቡ ማንነት የሚገርም ነው። በመሪዎቻችን ማንነት ሕዝቡ ማንነቱን ተጠልፎ መነጋገሪያ የሆነው የመሪዎቻችን ማንነት ነው። ማን ያውራ ስለ ደጉ ሕዝብ? ማን ያውራ በፍቅር ስለሚተሳሰበው ሕዝብ። ሲራብ አብልቶ፥ ሲጠማ አጠጥቶ፥ አብሮ ተቻችሎና ተጋብቶ ለዘመናት የሚኖረውና የሚያኖረው ሕዝብ ማን ማንነቱን ያራግብለት? ያደከመን በመሪዎቻችን ማንነት ላይ የተመሰረተ የፊት ለፊት እውነት እያወራን ስጋታችን መብዛቱ ነው። ሁሉም ዓላማውን የሚያራምደው ኢትዮጵያን የመሪዎቻችን ነፀብራቅ አድርጎ በመውሰድ ነው። ከላይ ላይ ከሚታየው እውነት ጀርባ የተደበቀውና በጊዜ ተፈትኖ ያለፈው ትልቁ ጥልቅ እውነት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቤተሰብነት ነው። 2ኛ/ የሀገር ልጅ የሚገርም ነው። መሪዎቻችን ሁሉ ሲታዩ ለየቅል ናቸው፦ ኢአዴግ፥ ግንቦት ሰባት፥ መድረክ፥ ሰማያዊ፥ ኦነግ፥ ወዘተረፈ። እንደገና ግልፅ ከሆነውና ከምናውቀው እውነት ጀርባ ያለውን የማይታየውን እውነት ለማየት ብንጥር ሁሉም የሀገር ልጆች ናቸው። ይህም በራሱ ክብር ነው፥ ምክንያቱም ከታላቁ ሕዝብ አብራክ የወጡ የሕዝቡ ልጆች ስለሆኑ ነው። የሀገር ልጆች ስለሆኑም በውስጣቸው ያለው እስከ ዛሬ ያልታየው ችሎታቸው ታሪክ ለመስራት አቅም አለው። እነዚህ የሀገር ልጆች ድንቅ የሆነው ችሎታቸውና እምቅ አቅማቸው እስካልተገለጠ ድረስ አንዱ ሌላኛውን ለማጥፋት መሮጣቸውን አያቆሙም። ይህ ያልተገለጠው አቅም በውስጥ የሀገር ልጅነት እውን እንደሆነ ሁሉ በገሀዱ ዓለም እውን ሆኖ እንዲወጣ ተአምር ይጠይቃል። ተአምር ማለት ሲደረግ ታይቶ የማይታወቅና፥ ይሆናልም ተብሎ ሊታሰብ የማይችል ነገር ሲሆን ነው። 3ኛ/ ውይይትና መግባባት የሚገርም ነው። በሀገር ልጆች ያለው እምቅ አቅም የሚገለጠው፥ በሕዝቡ ቆራጥ ግፊት መሪዎቻችን ውይይትና መግባባትን የችግራችን መፍቻ አድርገው መጠቀም ሲችሉ ነው። ይህ ተአምር የአገር ልጆችን እርስ በርሳቸው ተጨፍልቀው አንድ ወጥ እንዲሆኑ የሚያደርግ ሳይሆን፥ እያንዳንዳቸው ውይይትና መግባባትን ተክነውበት፥ ስልጣኑን ባለቤት ለሆነው ሕዝብ ማስረከብ የሚችሉበት መድረክ የሚፈጥር ነው። ተአምሩ ዲሞክራሲና እኩልነት አይደለም። እነዚህ እሴቶች ተአምራት ከሆነው ውይይትና መግባባት የሚገኙ ውጤቶች ናቸው። ይህም እንደ ድሮ በጠጉረ ልውጥ አሳላፊነት የሚካሄድ ሳይሆን በሀገር ልጆች ሽማግሌነት እውነትን ብቻ ዋና መሰረት አድርገው የሚተገብሩት ጉዳይ ነው። ፊት ለፊት ያለውን የውጭውን ብቻ ለሚያይ ሰው፥ ውይይትና መግባባት መንግስትን በስልጣን የሚያስቀጥል ጊዜ መግዣ እኩይ ተግባር፥ ወይም ተቃዋሚን በአቋራጭ ስልጣን ላይ የሚያስቀምጥ መሰሪ ድርጊት አድርጎ ይወስዳል። የማይታየውን እውነታ ጠጋ ብሎ ለማየት የታደለ ግን፥ ውይይትና መግባባት እስከ ዛሬ ያልተፈተነ ተግባር ሆኖ፥ የሀገር ልጅነትን ውበት ከመሪዎቻችን ውስጥ አውጥቶ እንደ ብሩህ ብርሃን የሚያስፈነጥቅና፥ ለሕዝብ የስልጣን በላይነት ተገዥዎች እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው። 4ኛ/ የሚጠበቀው ነገር የሚገርም ነው። ከእንግዲህ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የለም። ማንም ላይታመን፥ ሕዝቡ ራሱን ብቻ ሊያምን ተነስቷል። ስልጣን የሕዝብ ነው እያሉ በስሙ የሚነግዱ ከእንግዲህ በቃችሁ ተብለዋል። ስልጣን የሕዝብ መሆኑን የሚናገር ሳይሆን በሕዝቡ ለመመራት ራሱን የሕዝቡ ተከታይ የሚያደርግ ብቻ ይፈለጋል። ከትልቅ ትዕግስት በዋላ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሕዝቡ የተነሳው፥ ለመንግስት ስልጣኑን የሚያስረዝምበትን መላ ለማፈላለግ፥ ወይም ለተቃዋሚ የስልጣን ውርስ እንዲያደርጉ ለማመቻቸት ሳይሆን፤ መሪዎቻችን የሕዝቡን ድምፅ እንዲሰሙ እና ስልጣንን ለባለቤቱ (ሕዝብ) ማስረከቢያውን መንገድ እንዲፈጥሩ ነው። ፈሪሃ ፈጣሪ ያለው ይህ ሕዝብ አምላክ እንዳለለት ይታወቅለት። ኢሜል አድራሻ፦ [email protected]
1 Comment
|
Details
MemberZelalem Eshete, Ph.D.
Deeper Walk With God Book on Ethiopia
This book makes a case for a paradigm shift in our thinking on the matter of Ethiopia. Instead of feeling powerless in our usual political saga, ethnic divide, and religious tensions, the book motivates us to look deeper, rediscover our true identity, and arise to make change. The greater power of change is with the people. The world has heard enough of our suffering. Let's spotlight the other face of Ethiopia: To Be Known As We Truly Are.
The world has heard enough of our lack of civilization. Let's spotlight the other face of Ethiopia: We Are One Big Intelligent Family. The world has heard enough of our poverty. Let's spotlight the other face of Ethiopia: Going Global Together. |