ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
የኢትዮጵያ አምላክ ስጦታ የሆኑት ዶ/ር አብይ አህመድ የተነሱለት ራዕይ ከእኛ ኢትዮጵያውያን ተርፎ ለአፍሪካም በረከት የሚሆን ጭምር ነው። ፈጣሪ የሕዝብን የዘመናት ልመና ሰምቶ፤ ዛሬ በፍቅር ደስታ ተዐምር በሚያሰኝ ሁኔታ መላውን ሕዝብ አንድ እያደረገ ይገኛል። እኚህ ሰው ዲሞክራሲን አዋልደውና የአፍሪካን አንድ የመሆን ራዕይ ፈንጥቀው ከስልጣናቸው ዞር የሚሉ “ጉደኛና ታሪከኛ” መሪ እንጂ፤ አምላክ የሰጣቸውን የማያልፈው የኢትዮጵያ አባትነት ክብር፥ ለሚያልፈው የስልጣን ጥማት የሚሸጡ አይመስለኝም። ስለዚህ እኚህን የፍቅር ስብዕና የተካኑትን ጠ/ሚ፤ ለሁሉ ፍቱን መድሃኒት የሆነውን ተወዳጅ የመደመር አስተሳሰብ ማደናቀፍ በታሪክ የማይሽር ጠባሳ በራስ ላይ ያመጣል። ይህ ዓይነት ጠባሳ ኢትዮጵያዊ በሆነ ሁሉ ላይ እንዳይመጣ ሁላችንም የቻልነውን ያህል የማሻገር ስራ እንድንሰራ እንነሳሳ። የሕወሓት አመራር ዶ/ር አብይ አህመድን ከመምረጥ ሂደት ጀምሮ እስካሁን ድረስ፤ ራሱን በለውጡ ባቡር ላይ ሙሉ በሙሉ መቀላቀል ተስኖት፤ በመጀመሪያ ደረጃ ለራሱ፥ ቀጥሎም ለሀገሪቱ አስቸጋሪ ፈተና እንዳይሆን በሚያስፈራበት ሁኔታ ላይ እያለ መሆኑ ለሁሉም ግልፅ ነው። አስተውሉ፥ የትግራይ ሕዝብ አላልኩም። ደግሞም ሕወሓት አላልኩም። የሕወሓት አመራር ነው ያልኩት። የሕወሓት አመራር እስካሁን ለሁሉ መፍትሄ የሆነውን የዶ/ር አብይን የማሻገር ዕድል ሊገነዘቡት አልቻሉም። አሁንም ከተኙበት ነቅተው ከሠፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የለውጥ አራማጆች ለመሆን እንዲቀላቀሉና እንዲሻገሩ ሁላችንም በትዕግስት እየጠበቅናቸው ነው። የሆኖ ሆኖ የሕወሓት አመራሮች፤ ሕወሓትን ለጥፋት እንዳይዳርጉና የትግራይን ሕዝብ ትግል ታሪክ በዜሮ እንዳያስኬዱ፤ የትግራይ ወገኖቻችንና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ድምፅ ተሻገሩ የሚል ድምፅ እናሰማቸው። የሕወሓት አመራሮችም ራሳቸውን ከእልከኝነት አፅድተው፤ ድርጅታቸውን ለወጣት የለውጥ አራማጆች በመልቀቅ፤ የሕዝብን አንድነት እንዲጠብቁ አደራ እንላለን። መፅሀፉ አንገቱን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል እንደሚል፤ ይህንን ለማስተዋል እንዲችሉ ሁላችንም ላሰበንና ሊባርከን ለተነሳው ፈጣሪ በፀሎታችን እናቅርባቸው። ኢትዮጵያ የጀመረችው ጉዞ የተለመደው በደም የተለወሰ አብዮት አይደለም። ምናልባትም ለዓለም የመጀመሪያው የሆነና የአምላክ እጅ ያለበት የ “ፍቅር ያሸንፋል” የይቅርታና የመደመር ተዐምራዊ አካሄድ ነው። ታዲያ አሁንም የአምላክ እጅ በምህረት እንደተዘረጋ፤ በይቅርታና በፍቅር ተያይዘን እንድንዘልቅ ሁሉም ወደ ልቡ ይመለስ። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ፤ ይባርካታልም። ኢሜል ethioStudy@gmail.com
1 Comment
ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
አዲሱን የፍቅርና የመደመር ጉዞ በአብሮነት ስንያያዘው፥ አንድነታችንን የሚያንፀባርቀው ባንዲራችን ግን በሁለት ጎራ ተከፍሎ ያሳብቅብናል። ይህንን ችግር ለመፍታት የባንዲራችንን ጉዳይ በሦስትዮሽ ከፍለን ማየት ያስፈልገናል። ምክንያቱም የባንዲራችን ምስጢር ምጡቅ ስለሆነ፤ እንዲህ በአንድ ጊዜ ምንነቱ ላይ መድረስ አንችልምና። የባንዲራችንን ረቂቅ ምስጢር ከኢትዮጵያዊነት ማንነታችን ረቂቅ ምስጢር ጋር የተያያዘ ነው። ስለዚህ በየረድፉ በሂደት የሚገለፀውን የባንዲራችንን ክብር እንመልከትና መግባባት ላይ እንድረስ። መነሻ ባንዲራችን፦ የዛሬው ባንዲራ የታሪካችን ምልክት ታሪክን ተሻግሮ የመጣው አረንጓዴ ብጫ ቀዩ ባንዲራ ነው። የቀድሞ መሪዎቻችን ስማቸውን የሚወክል ፊደል በዚሁ ባንዲራ ላይ ያስቀምጡ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። በቅርቡም ጃንሆይ ዘውድ የተጫነበትን አንበሳ አስቀምጠውበት ነበር። ኮሎኔል መንግስቱም የኮሚኒስቶቹን ምልክት አምጥተውብን ተደበላልቆብን ነበር። የትላንትናውም ኢሕአዴግ አሁን የሚታየውን ኮከብ ጭነውልናል። አርማው ይቀያየር እንጂ፤ ታሪካዊው አረንጓዴ ብጫ ቀዩ መሰረታዊ ባንዲራ ምንም ይሁን ምን ትውልድን ተሻግሮ በሁሉም ዘንድ ምንነቱ ሳይቀየር ዛሬ ደረሰ። አንድነታችንን ይህን ነጠላ ባንዲራ (የነገስታት መገለጫ የሆኑትን ምልክቶችን ሁሉ ትተን) እንደ መነሻ ባንዲራ ዛሬ ብንጠቀም መልካም መግባባት ይሆንልናል። መድረሻ ባንዲራችን፦ የነገው ባንዲራ የፍሬያችን ምልክት ከዚህ በፊት እንደሆነው ትውልድ የማይሻገር ምልክት ከማድረግ ስህተት ለመጠበቅ፤ ለወደፊቱ በባንዲራው ላይ ለውጥ የማምጣት ሂደት ከተለመደው ለየት ማለት አለበት። 1ኛ/ ይህን ነጠላ ባንዲራችን (ምንም ምልክት የሌለበት) ለመለወጥ ከመሞከር በፊት በቅድሚያ ትውልድ የሚሻገር አዲስ ታሪክ መስራት አለብን። ወጡ ሳይወጠወጥ እስክምባው ላይ ቂጥ እንዳይሆንብን፤ ባንዲራውን ሳንነካ መጀመሪያ ታሪካችንን በበጎነት እንቀይር። ይህም አዲሱ ታሪካችን ትውልድ እስኪሻገር እንጠብቅና ፍሬውን እንይ። ያኔ አዲሱን ታሪካችንን የሚመጥን ምልክት፤ ባንዲራችን ላይ እናድርግ ብንል ያምርብናል። 2ኛ/ ባንዲራ ለመቀየር በሕዝብ ተሳታፊነትና በሪፈረንደም እጅግ አብላጫ በሆነ ድምፅ ይከናወን ዘንድ ይገባል። እንኳን በዲሞክራሲ ያልተመረጠ መንግስት ይቅርና፤ በዲሞክራሲም የተመረጠ መንግስት ቢመጣ፤ ይህንን ታላቅ ባንዲራ የመቀየር ሃላፊነት መውሰድ ያለበት መላው ሕዝብ ብቻ ነው። ስለት እንሣል። ዛሬ ተአምራዊ ጉዞ ያስጀመረን አምላክ እንዲሁ ተዐምሩ እየበዛልን ቢቀጥልስ? ለዘመናት የምንሰማው “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለው ተስፋ እውነት ሆኖ የጀመርነው የፍቅርና የይቅርታ መንገድ የተቃና ቢሆንስ? የምንመኘው ዲሞክራሲ ነገ ዕውን መሆኑ ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያኑ የሚቀኑበት ቢሆንስ? ፍቅራችንና አንድነታችን ጎልብቶ፤ ዘረኝነት በወንድማማችነት ተተክቶ፤ በአምላክ ስር ያለን አንድ ቤተሰብ ሆነን ብንገለጥስ? ፀሎታችን ተሰምቶ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ቢባርካትና የሁሉ ዓይን ማረፊያ ቢያደርጋትስ? በውኑ ያኔ የረዳንን አምላክ የሚገልጥ ምልክት በባንዲራችን ላይ እናደርግ ይሆንን? ኢትዮጵያ ከጥሪዋ ጋር የሚሄድ አርማ (የተዘረጉ እጆች) በባንዲራችን ላይ የሚያርፍበት ዘመን ይምጣልን የሚል ምኞት አለኝ። ይህ ዓርማ ታሪካዊ በሆነው ባንዲራችን ላይ ቢቀመጥ ሊሰጠን ያለውን በረከት በጥቂቱ እንመልከት።
ስጦታ ባንዲራችን፦ የከነገ ወዲያው ባንዲራችን የአፍሪካ ተስፋ ምልክት ራዕያችን እየሰፋ ነው። መሪያችን የአፍሪካ ድንበር የውጭ ሰዎች የሰጡን እንጂ አፍሪካ አንድ ሕዝብ ነን እያሉ ነው። ራዕያቸው ሰምሮላቸው የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ብሎም መላው አፍሪካ አንድ ስትሆን፤ የአፍሪካ ባንዲራ ምን ይሆን እንደሆነ መገመት አያስቸግርም። ትላንት በአድዋ የተሰራው የአፍሪካ ድል፤ ለብዙ አፍሪካ ሀገሮች የኢዮጵያን ባንዲራ ቀለሞች በኩራት እንዲዋሱ አድሮጓቸዋል። ትላንት በደም የተሰራውን የአድዋ ታሪክ ይበልጥ የሚያደምቅ፤ ዛሬ ደግሞ በፍቅር እየተሰራ ያለው የዶ/ር አብይ ታሪክ ለዳግመኛ የአፍሪካ ድል እያዘጋጀን ነው። ኢትዮጵያ ሞዴል መሆንን ከተያያዘችው፤ የአፍሪካ ተስፋ ምልክት መሆኗ አይቀሬ ነው። ያኔ የአፍሪካ ሕዝብ ባንዲራችንን በስጦታ እንድንሰጣቸው ይጠይቁናል ብዬ እገምታለሁ። አርቲስቱ ቴዲ አፍሮ ባንዲራችን የቃል ኪዳን ምልክትነቱን ሊያሳየን፤ ባንዲራችን በሰማይ ላይ ታየ ብሎን የለ? ታዲያ የአምላክ እጅ የገባበት ይህ ባንዲራ ሊያመጣ ያለው በረከት ምጡቅነት እጅግ የጠለቀ ነው። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ፤ ይባርካታልም። ኢሜል፦ ethioStudy@gmail.com ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
በቅድሚያ የፍቅር ሐዋርያና የኢትዮጵያ ማንዴላ ለሆኑት ዶ/ር አብይ፤ በሕይወታቸው የተቃጣውን እኩይ ሴራ ስንመለከት፤ ከደጋፊነት አልፈን በፍጥነት ወደ ረዳትነት መሸጋገር ሀገራዊ ግዴታ እንደሆነ መገንዘብ ይገባናል። ለማመንታት ጊዜ የለም። በቃ። በዚህ የመደመር መርሀ ግብር ውስጥ መከናወን ያለባቸው አራት አብየት ጉዳዮች አሉ። 1ኛ/ ጥናት፦ የኢትዮጵያን አስተዳደር በተመለከተ ያስከተለውን ግጭትና የሕዝብ መፈናቀል መዘዝ ይጠና ያሉትን ዶ/ር አብይን በዚህ ጥናት ላይ መሳተፍና የመፍትሄው አካል መሆን። ባለፈው 44 ዓመታት የሞከርናቸውን የለውጥ መንገዶች በሙሉ መፈተሽና ወደ ብርሃን ማምጣት። 2ኛ/ ትምህርት፥ መከላከያው፥ ፍርድ ቤት፥ ሚዲያ፥ ምርጫ ቦርድ የመሳሰሉት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ገለልተኛ ሆነው ለዲሞክራሲ ዘብ እንዲቆሙ ዶ/ር አብይ የጀመሩትን የማስተማር ሂደት ላይ ተባባሪ በመሆን የጨለማውን ጊዜ አካሄድ በእውቀት ብርሃን መግለጥ። ጊዜው የፍቅር ይቅርታና መደመር ነውና ይህንን አዲስ ርእዮተ ዓለም በሁላችንም ዘንድ እንዲሰርፅ መማርና ማስተማር። 3ኛ/ ለውጥ፥ መከላከያው፥ ፍርድ ቤት፥ ሚዲያ፥ ምርጫ ቦርድ የመሳሰሉት መዋቅራዊና ሕጋዊ ለውጦች ላይ በሚደረገው ሂደት በተሳታፊነት ራስን በማቅረብ፤ ለውጡ ከውስጥ ወደ ውጭ እንዲዘልቅና ለተዐማኒ ምርጫ መሰረት እንዲጥል ማድረግ። ሕዝብም በነፍስ ወከፍ ልውጠትን በማካሄድ ለአዲሱ የኢትዮጵያ የብርሃን ዘመን መዘጋጀት። 4ኛ/ ፀሎት፥ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ተዐምራዊ ጉዞ የኢትዮጵያ አምላክ እጅ ያለበት ስለሆነ፤ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ እኩይ እንዳያኮላሽብን በየቤተ እምነታችን ሆነን ወደ ፈጣሪ መጮህን ማብዛት። ይህም የፀሎት አጀንዳ በገሃድ ስናደርግ እርስ በርሳችን በፍቅር ሰንሰለት እያያያዘን ወደ አንድነት ያመጣናል። ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲ በሚያስኬድ ሽግግር ላይ ትገኛለች። ለዚህ የሽግግር ሂደት የሽግግር መንግስት ማቋቋም ለዛሬ መፍትሄ አይደለም። ነገር ግን የሚያስፈልገው በሕዝብ ዘንድ ተዐማኒ የሆኑትና የሽግግር ድልድይ ከሆኑት ከዶ/ር አብይ ጋር መደመር ነው። ይህንን አስተሳሰብ ለመፈተሽ እንዲረዳን ከዚህ የሚከተሉትን 8 ነጥቦች አነሳለሁ። 1ኛ/ በአብሮነት መላ መፍጠር። መፍትሄን እንደ ስጦታ ከመጠየቅ በአብሮነት መላ መፍጠር ይሁንልን። ከእኚህ የኢትዮጵያ ልጅ ዶ/ር አብይ ጋር ተያይዘን በመስራት፤ የዶ/ር አብይ የሽግግር ድልድይ ጋር መደመር ይሻለናል። አጋርነትን መግለፅ ማለት በሩቅ ሆኖ “ጥሩ ጅማሬ ነው” ብሎ መደገፍ ብቻ ሳይሆን፤ ቀረብ ብሎ ዲሞክራሲ እንዲወለድና ለእውነተኛ ምርጫ ተአማኒነት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ በአብሮነት ማሳለጥ ነው። 2ኛ/ የዶ/ር አብይ አህመድ ስብዕና። ዶ/ር አብይ በተለየ መልኩ የኢትዮጵያዊነትን ገፅታ እያንፀባረቁ ይገኛሉ። አንድም በፓርላማ ሆነው ሲናገሩ አንበሳ ናቸው ያሰኛል። ደግሞ የእርቅን ዘንባባ ይዘው ለውስጥም ለውጭም የፍቅር ጥሪ ሲያቀርቡ ርግብ ናቸው ያሰኛል። ከዚህ እልፍ ስንል ደግሞ ተበጣጥሰንና አጥር አበጅተን ስንባላ፥ ከኢትዮጵያ አልፈው የምስራቅ አፍሪካ ድንበር አልታያቸው ብሎ አንድ አፍሪካን ሲያልሙ፤ ምድር ላይ ትል ከሚለቅመው ዶሮ ይልቅ ከፍ ብሎ የሚበረው ንስር ናቸው ብለን እንደመድማለን። የኢትዮጵያዊነትን ምንነት በስብዕናቸው የሚያንፀባርቁትን እኚህን የኢትዮጵያ ልጅ፤ ጥሪያቸውን ተቀብለንና በወንበር ዙሪያ ተቀምጠን እውነተኛ ዲሞክራሲ ለማስወለድ ለእርሳቸው የአዋላጅነት ዕድል ለመስጠት የሚታመኑ ናቸው። ምክንያቱም በዶ/ር አብይ አህመድ አመራር ምክንያት ሕዝብ በአደባባይ ፍቅሩን ሰጣቸው። እሳቸውም የሕዝብን ድምፅ በመስማት ከምንም በላይ ለሕዝብ ታማኝነታቸውን በየዕለቱ ሲገልጡ ይታያሉ። 3ኛ/ ኢትዮጵያ የተዐምር ሀገር። ለመሆኑ የኢትዮጵያ ጉዞ በዚህ አጭር ጊዜ ያየነው ከተለመደው ወጣ ያለ ነው። ተዐምር ሆኖብን በእውነት የኢትዮጵያ አምላክ አለ አልተባለምን? ታዲያ በተዐምር የተጀመረው ይህ ሂደት በተዐምራዊነቱ እንዲቀጥል እምነት ልናጣ አይገባም። በሁሉም ጎራ የተሰለፉትን የኢትዮጵያ ድንቅዬ ልጆቿን አሳትፋ፤ ዓለም ከዚህ በፊት ያላየውን አዲስ መንገድ ኢትዮጵያ ማሳየት ትችላለች። ሌሎች ሀገሮች የኢትዮጵያ መንገድ ብለው የሚጠሩት አካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመቀየስ እንነሳ። 4ኛ/ የትግሉ ባለአደራና ጠባቂ ሕዝብ ነው። እናውቅልሃለን ብለን ሕዝቡን ከራሳችን ጎን ማሰለፍ ከእንግዲህ አይቻልም። የሚያዋጣው ራሳችንን ከሕዝብ ጎን ማሰለፍ ነው። የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ባለቤት ሕዝብ ነው። ባለአደራውም ሕዝብ ነው። ከእንግዲህ ሕዝብ ራሱ ንጉስ ሆኖ በምርጫ ካርድ አገልጋይ የሚሆነውን መንግስት እስኪመርጥ ድረስ አያርፍምና፤ ሁላችንም የሕዝብን ድምፅ እያደመጥን ከዶ/ር አብይ አመራር ጋር መንገዳችንን በአብሮነት መጓዝ ጥሩ ነው። 5ኛ/ የራስን የቤት ስራ መወጣት። ድሮ ድሮ ምርጫ ስለሌለ ሁሉም ተቃዋሚ መሆን ነበረበት። ግማሹ በሰላማዊ ትግል፥ ሌላው በትጥቅ ትግል ግዴታ ስለሆነ ተሰለፈ። ተወያይቶ ሀሳብን ያማከለ ህብረት በማድረግ ለመቀናጀት ፋታ አልነበረውም። ዛሬ ግን ሁኔታው እየተቀየረ ነው። ጊዜው የተበታተነው ተፎካካሪ በአስተሳሰብ ዙሪያ ሃይሉን በማቀናጀት ፈርጠም ያለ ተፎካካሪ በመሆን መቅረብ የሚጠበቅበት ወቅት ነው። ጊዜው የትግል ስልት የሚያስቀይር ነው። የተፎካካሪው ውበት እንዲወጣና እንዲያስደምመን፤ የራስን የቤት ስራ መወጣት ይጠይቃል። ታዲያ ይህንን የራስን የቤት ስራ ለመስራት ጥድፊያ ላይ እንሁን። 6ኛ/ ልዩ ብቸኛ አጋጣሚ። ሁልጊዜ ከዜሮ መጀመር ለአሁኑ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ መልስ አይደለም። ያለውን ስርዐት ድምጥማጡን አጥፍቶ፤ አዲስ ሽግግር መንግስት እናቋቁም ብለን ከምንታገል፤ በሕዝብ የፀደቀውን የዶ/ር አብይ አህመድ ድልድይ የመሆን ልዩ ብቸኛ አጋጣሚ በመጠቀም፤ ወደ እውነተኛ ምርጫ መሄድ ላይ ማተኮር ይሻላል። ይህን የተጀመረው የለውጥ መንገድ እንዳይሰምር በመንግስትና ኢህአዴግ ውስጥ ሆነው እንቅፋት የሚሆኑትን ወንድሞቻችንን አይጠቅማችውም ብለን ልንሞግታቸው ያስፈልጋል። 7ኛ/ ሕዝብ የወለደው አመራር። ብዙ ጊዜ የሽግግር መንግስት ከአምባገነን መሪ ለመላቀቅ፤ ወይም መንግስት በአመፅ ምክንያት መግዛት ሲሳነውና ሲፍረከረክ፤ ከዜሮ ለመጀመር ሲገደድ የሚደረግ ክስተት ነው። አሁን ያለው አመራር ግን በሕዝብ ምርጫ የመጣ ባይሆንም በሕዝብ ትግል የተወለደ ነው። እነ አቶ ለማ፥ አቶ ገዱ፥ አቶ ደመቀና ሌሎችም የለውጥ አራማጆች ተጋዳይነትና በኢትዮጵያ ወጣቶች ደምና እንግልት የመጣ ነው። ስለዚህ ይህንን አክብሮ ከዚህ ሕዝባዊ ከሆነ አመራር ጋር መደመርና ሌሎችም እንዲደመሩ ተግቶ መስራት መልካም ነው። 8ኛ/ አዲስ ጊዜ፥ አዲስ አመለካከት። ሁሉም የሽግግር መንግስት እውነተኛ ዲሞክራሲ እንዳመጣ ታሪክ አይነግረንም። ትላንት በጨለማው ዘመን የሽግግር መንግስት ስንል ከርመን፥ ዛሬ ጊዜው ተቀይሮ ብርሃን ሲወጣም፤ ይህ የድሮ ሀሳባችን ጊዜውን ይመጥነው እንደሆነ ሳንለካው፤ ትላንት የፃፍነውን ወረቀት ዛሬም ያንኑ ብቻ ማንበብ እውቀት አይሆንም። ከሩቅ በመሆን፤ የማያባራ ትዕዛዝ ለዶ/ር አብይ ከመስጠት፤ ጠጋ ብለን በጋራ የምንስማማበት የዲሞክራሲ ውልደት ፍላጎት ላይ ተመስርተን ወደ ውይይት ማምራት ይሻላል። የኢትዮጵያ ልጆች ከሩቅ ከቅርብ ለዶ/ር አብይ ተልዕኮ መሳካት ሲረባረቡ ማየት፤ ይህ ህዝብ ታሪክ ሊሰራ ቆርጦ መነሳቱን ያሳያል። አብሮ መብላት ብቻ ሳይሆን፥ አብሮ መስራትም የተካነ እንደሆነ ሊያስረግጥ ተነስቷል። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ፤ ይባርካታልም። ኢሜል፡ ethoStudy@gmail.com ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
ፈጣሪ የሰጣት ለኢትዮጵያ ምድር ስጦታ አድርጎ ታሪክ የሚቀይር ለያዘን አባዜ ጥላቻን የሚያሽር መድሃኒት ተገኘ ስብዕናው ፍቅር እንደ ንጋት ብርሃን ጨለማውን ገፎ፥ ስጋትን አምክኖ ሁሉን በአንድ አቅፎ፤ ራዕዩን ሰንቆ አዋላጅነቱን፥ ደረሰ ያገር ልጅ ሊሆንልን ፍቱን። ሙጥኝ የሚል መዥገር ነው ብሎ መገመት፥ እንዴት ይታሰባል ለስልጣን የሚሞት፥ አባት መሆን ሲችል ለኢትዮጵያ እናት። የዛሬ ሁለት ዓመት ቁርጥ ነው ነገሩ፥ እውነተኛ ምርጫ ሊታይ በሀገሩ። ፈጣሪ የሰጣት ለኢትዮጵያ ምድር፥ ዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ምስጢር፤ ኢትዮጵያን አሻግሮ ሕዝብ ንጉስ ሲሆን፥ እኛም በተራችን ስጦታ አድርገን፤ እርሱን እንድንሰጥ ለምስራቅ አፍሪካ፥ የአብይ ስራ ይሁን ጥቁር የሚያፈካ። ይሄ ሁሉ ጉዞ ፊት እየጠበቀን፥ የቀን ጅቦች መንገድ ቆመው ሲሰልሉን፤ ጣጣ ስናበዛ፥ እንዲሁ እንደዋዛ፤ እያቅማማን ስናመነታ፥ እንዳናስመታ እንዳንመታ። ኢሜል፡ ethioStudy@gmail.com ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
ዶ/ር አብይ አህመድን ምን እንላቸዋለን? ከአሁን በፊት መሪዎቻችንን ለመግለፅ የተጠቀምንባቸውን ቃላት ሁሉ የሚያልፉ ሆኑብኝ። ጉደኛ የሚለውን ቃል የመረጥኩት፥ ያልተለመደና ያልታየ ነገርን ስለሚገልፅ ነው። በሌሎች ስንቀና የኛም ተራ ደርሶ ይሆንን? ደቡብ አፍሪካ ማንዴላ ነበራት፤ ሕንድ ማህተመ ጋንዲ ነበራት፤ አሜሪካ ጆርጅ ዋሽንግተን ነበራት። ኢትዮጵያ ዶ/ር አብይ ደረሰውላት ይሆን? ፋታ እንስጣቸው እያልን ስናወራ፤ እርሳቸው በድርጊታቸው አንዱን ሳናጣጥም ሌላ እየጨመሩ በመልካምነት ፋታ አሳጡን። ቀድመው ያሞገሱትን ማማት ይቸግራል ብለን፤ ተስፋን በስጋት ሰንቀን ዳር ቆመን በጥርጣሬ የምናይ ሁሉ ጉድ ፈላብን። ዛሬ ዛሬ ተስፋ ስጋትን እያሸነፈ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ለዶ/ር አብይ ድጋፍ እየጎረፈ ነው። ትላንት እንዳንጨራረስ እየፈራን ከዚህ አጣብቂኝ ማን ያወጣናል ስንል ነበር። የማይታለፍ የለም ያ ታለፈና፤ አሁን ዶ/ር አብይ በፍቅርና በይቅርታ ሁሉንም እየማረኩና እያስደመሙ፤ በደስታም እያሰከሩ በሚገርም አዲስ አካሄድ ኢትዮጵያን እያሻገሩ ይገኛሉ። ግን ቆም ብሎ ለሚያስተውል፤ ይህ ትዕይንት ከስጋና ደም ስራ በላይ ነው። የኢትዮጵያ አምላክ በምህረት እርሱ ራሱ ምድራችንን በፈውሱ እየጎበኘ እንደሆነ ለአስተዋይ ሰው ምንም ጥርጥር የለውም። አምላክ ደግሞ በስራ ላይ ሲሆን፤ ጠላት ለማሰናከል ሙከራ ያደርጋል እንጂ ፈጣሪን ያደናቅፈዋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። ያልተጠበቀው የኢትዮጵያዊነት ውበት ነገ እጅግ ደምቆ ሲበራ ልናይ ከሆነ፤ የማይጨበጥ ሕልም የሆነብን ዲሞክራሲ ነገ እንደ እለት እንጀራችን የምንመገበው ዕውነታ ሊሆን ከሆነ፤ ዛሬ የሚገፋፉትና የሚጠላለፉት ፖለቲከኞች ሁሉ በጠረጴዛ ዙሪያ ሆነው በወንድማማችነት መንፈስ የአስተሳሰብ ፍጭትና ፍትጊያ ሲያደርጉ አይተን ለመሆኑ እንዲህ ያሉ ድንቅየዎች ከየት መጡ እስክንል ድረስ የሚያስገርሙን ከሆነ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሜዳውም ይሄው ፈረሱም ይሄው በሐቅ መሪህን ምረጥ ተብሎ ጉድ የሚባልበት ጊዜ ሊመጣ ከሆነ፤ እኛስ የየራሳችንን የኑሮ ብልሃታችንን እንደለመድነው ከዚህ በሁዋላ ማስኬድ እንዴት ይቻለናል? ዛሬ አይደርስ መስሎን ራሳችንን ለኢትዮጵያ የተዘጋጀን እንደሆነ ለመጠየቅ ሀሳቡም የለንም። ዛሬ ዓይናችንን ዶ/ር አብይ ላይ አተኩረን ራሳችንን ከሃላፊነት አሰናብተናል። ቁምነገሩ ኢትዮጵያ ልትነሳና ልትደምቅ፤ ይህንንም መቀልበስ በማይቻል ጎዳና ላይ ዶ/ር አብይ በብልሃት የተሞላ የጥድፊያ ጉዞ ላይ ያሉ ይመስላል። ታዲያ ለዚህ የመታደስ ዘመን ራሳችንን በመስዋዕትነት ለመስጠት እያሰብን ነን ወይ? ኢትዮጵያ የሚሞትላት ሳይሆን በመስዋዕትነት በመኖር ለችግሯ ሊደርስላት የሚችል ዜጋ የምትፈልግበት ጊዜ እየመጣ ነው። ለመልካም ኑሮ ሀገራችንንና ምድራችንን ትተን የተሰደድን ሁሉ፤ ለምድራችን ፈውስ ለመሆን ምቾትን ንቀን፥ ከሕዝባችን ጋር መከራ በመቀበል የደስታው ተካፋይ ለመሆን ለኢትዮጵያ ዝግጅት ማድረግ የምጀምርበት ወቅት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትም ቢሆኑ በፅድቅና በእውነት ለሕዝብ አገልጋይ በመሆን ራስን ከምቾት አፋተው ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት የደስታው ተካፋይ ለመሆን ለኢትዮጵያ ዝግጅት የሚያደርጉበት ጊዜ ነው። ዶ/ር አብይ ለኢትዮጵያ እየሰሩ ያሉትን እየወደድንና እያወደስን ባለበት በዚህ ወቅት፤ ለዶ/ር አብይ ኢትዮጵያ ራሳችንን በማዘጋጀት እንዲሆን ፈጣሪ ይርዳን። በመስዋዕትነት በምድረ ኢትዮጵያ በስራ ተጠምደን፤ የሀገራችንን ታሪክ በራሳችን ትውልድ ዘመነ ጊዜ ለውጠን በማየት ከዚህ ዓለም አልፈን፤ ዶ/ር አብይ እንዳሉት ያኔ እኛም በክብር ኢትዮጵያ እንሆናለን። ዶ/ር አብይ “ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ” ብለው ሲያውጁ፤ ያኔ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ለሰማይ አደራ ሰጥተው ራሳችንን ለተዐምሩ እንድናዘጋጅ ልባችንን ማነሳሳታቸው ነበር። እንደተባለውም ፈጣሪ ኢትዮጵያን ሊባርክና ያሳለፍነውን የመከራ ዘመን ሊያስረሳን የተስፋ ጭላንጭል ከጊዜ ወደ ጊዜ ቦግ እያለ እየተጨመረ በመብራት ላይ ይገኛል። ለዚህ አስደናቂ የታሪክ ዕድል ራሳችንን ለኢትዮጵያ ለማዘጋጀት መዘርጋት የሚገባን ይመስለኛል። ዶ/ር አብይ የአምላክን በረከት ከመጥራት አኳያ በንፅፅር የንግግራቸው ማሳረጊያ አድርገው የሚጠቀሙበት ሌላ ሀሳብ አላቸው። ያም፦ “ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ ተከብራና በልፅጋ ለዘላለም ትኑር” የሚለው ቁምነገር ነው። ፈጣሪም ልመናችንን ሰምቶ እየጎበኘን ባለበት ሁኔታ፤ ዶ/ር አብይም ታማኝ ሆነው ራሳቸውን ለተባረከች ኢትዮጵያ ራሳቸውን እየሰጡ ባለበት ሁኔታ፤ እኛስ ለኢትዮጵያ ትንሳዔ ጥረት ለማድረግ ተዘጋጅተናል ወይ? እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ። ይጎበኛታልም። ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
በ 44 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ መሪ በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ “ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ” እያሉ ንግግርዎን ሲያሳርጉ አይቶ ሕዝበ ኢትዮጵያ በደስታ ተሞልቷል። እኔ ግን እያሉ ያሉት ይህ የማሳረጊያ ቃል በሕዝብ ፊት ብቻ ሳይሆን በአምላክ ፊት ምንና ምንን በሃላፊነት ሊያስጠይቅዎ እንደሚችል የነገሩ ክብደት እጅግ አሳስቦኛል። የፈጣሪ ስም ከተነሳ ዘንዳ፥ ይህ ፈጣሪ የሚሰጠን በረከት ምንነት ይታወቅ ዘንድ ያስፈልጋል። “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ሲባል ዝንተ አለም አሳልፈን ዛሬን ደረስን። እስከ ዛሬ “ትዘረጋለች” ከማለት አልፈን “ዘረጋች” ወደማለት ሳንሸጋገር ሦስት ሽህ ዓመታት ጠበቅን። በዚህ ፅሁፌ ይህ 3000 ዓመታት ያስቆጠረው ትንቢት ተፈፀመ የሚያስብለው ሁኔታ ምን እንደሆነና፤ የፈጣሪን በረከት የጠየቁት እርስዎ ስለዚህ በረከት ሊኖርዎት የሚገባውን ግንዛቤ ለመጠቆም እሞክራለሁ። የዚህ ጉዳይ ተጠያቂነት ሁላችንንም የሚመለከት ስለሆነ የኛን ድርሻም ለማመላከት እሞክራለሁ። ይህ ጉዳይ ከሃይማኖት የሚወግን አይደለም። ሃይማኖት የግል ነው፤ ሀገር የጋራ ነው። ሁሉም ሰው ልቡ የፈቀደውን እምነት በነፃነት እንዲለማመድ አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠው ነፃ ምርጫን ነው። ስለዚህ መንግስት ሁሉንም ሃይማኖቶች ያለ አድልዎ በእኩልነት የሚያስተናግድ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ ልጆቿ በተለያዩ ቤተ እምነት ጥላ ስር ናቸው። ነገር ግን ባብዛኛው ሁሉም ፈሪሃ ፈጣሪ እንዳላቸው መገንዘብ ይቻላል። ሰላምታ በተሰጣጡ ቁጥር እንኳን ይህንን ፈጣሪ በሰላምታቸው ውስጥ ሳያስገቡ አያልፉም። የጥንት ነገስታት የአምላክን ስም እንደሚጠሩ ሁላችንም የምናውቀው እውነት ነው። የአምላክን ስም ሲጠሩ ግን የኢትዮጵያን መለኮታዊ ጥሪ ያማከለ አልነበረም። እነዚህ ነገስታት የኢትዮጵያን መለኮታዊ ጥሪ አግተው፤ በምትኩ መለኮታዊ ጥሪን በራሳቸው ዘውድ ላይ እንዲያጠነጥን አደረጉ። ስለዚህም የሰለሞን ስረወ መንግስት በመባል የሚታወቀውና የንግሥና ስልጣናቸውን ከእስራኤሉ ንጉሥ ስለሞንና ኢትዮጵያዊቷ ንግስት ሳባ የዘር ቆጠራ ጋር ያቆራኙ በርካታ ነገስታት በምድራችን እንደ ነገሡ ታሪክ ይነግረናል። ከዚህም በላይ የዛጉዬ ስረወ መንግስት የሚባለው የንግስና ስልጣናቸውን ለማረጋገጥ በእስራኤሉ ሙሴና ኢትዮጵያዊቷ ሲፓራ ዘር ቆጠራ ይደገፉ እንደነበር ይታወቃል። የኢትዮጵያ መለኮታዊ ጥሪ ግን በአንድ ሰው መሪና በእርሱም ንግስና የሚተረጎም አይደለም። ኢትዮጵያ (ሕዝቧ ሁሉ እንደ አንድ ሆነው) እጆቿን እንደምትዘረጋ ታየላት። የኢትዮጵያ ጉዳይ ከእስራኤል ታሪክም የተለየ ነው። የእስራኤል ታሪክ በግለሰብ ላይ ያጠነጠነ ነበር። ጥንት አንድ ግለሰብ የሆነው አብርሃም እጆቹን ወደ ፈጣሪው ስለዘረጋ፤ ዛሬ አይሁድ ሙስሊምና የክርስትና እምነት ተከታዮች ሁሉም አብርሃምን አባታችን ነው ብለው እንደ አዕማድ ያዩታል። የኢትዮጵያ ታሪክ ግን በሕዝብ ላይ ያጠነጠነ ነው። ስለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ሆኖ፤ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ በዘረጋች ጊዜ፤ ዓለም ሁሉ በምሳሌነት የሚያያት ምድር እንደምትሆን ነገን የሚደርስ ሰው የሚያየው ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ አብሮነት (መደመር) እንደ ዘር ሆኖ የአፍሪካን አብሮነት (መባዛት) ይፈጥር ዘንድ ማን ያውቃል? የኢትዮጵያን ነገሥታት ታሪክ የተደመደመው በጃንሆይ ንግሥና ነበር። ከዚያ በሁዋላ እስከ ዛሬ ድረስ ያሉት መንግስታት ራሳቸውን ንጉሥ ብለው አይጥሩ እንጂ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለስልጣን ሆኖ አገልጋዩ እንዲሆን መንግስትን ለመምረጥ ስላልታደለ፤ እነዚህ መንግስታት ንጉሦች እንደሆኑ መቁጠር እንችላለን። በዐመፅ ወይም በውርስ ነግሠዋልና። የኢትዮጵያ መለኮታዊ ጥሪ መቼ ይፈፀማል? ይህ መለኮታዊ ጥሪ እንዲፈፀም አንድ መንግስት አዋላጅ መንግስት ለመሆን መወሰን አለበት። ይህም አዋላጅ መንግስት ስልጣንን ለሕዝብ አስረክቦና ሕዝብን ንጉሥ አድርጎ፤ ንጉሥ የሆነው ሕዝብ በተራው አገልጋይ የሚሆነውን መንግስት በሐቅ ምርጫ እንዲመርጥ ዕድል ሲያገኝ ነው። ያኔ ይህ ንጉሥ ለመሆን የሚታደለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በምርጫው ፈጣሪን የምድራችን ንጉሥ እንደሆነ ዕውቅና ለመስጠት ፋታ ያገኛል። ያኔ ኢትዮጵያ እጆቿን ዘረጋች ተብሎ የእፎይታ ዘመን ጅማሬ ይሆንልናል። ሃይማኖትና መንግስት ለየቅል ሆነው እና ክህደት ተስተናግዶ ሲያበቃ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈጣሪ ኢትዮጵያን እንዲባርክ በባለስልጣናት ጉባኤ የተጠየቀበት ጊዜ ቢኖር ዛሬ ነው። ዶ/ር አብይ አህመድ “ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ” በማለት ለሚቀጥሉት መሪዎቻችን ፈር ቀዳጅና ፋና ወጊ ሆነዋል። ይህ አባባል የራስዎን ግንዛቤ እንደ ግለሰብ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፤ በሕዝብ ልብ ውስጥ ያለውን የጋራ ግንዛቤ ማስተጋባትዎ እንደሆነ ጭምር መቆጠር አለበት። ከእንግዲህ የመንግስትም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ይህንን የፈጣሪ በረከት ለመጠየቅ ህሊናቸው ብቻ ፍቃድ ይስጣቸው። ይሁንና ከእነርሱ በላይ ባለስልጣን የሆነ የኢትዮጵያ አምላክ እንዳለ ተዐምረኛዋ ኢትዮጵያ ይታወቅላት። ታዲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዶ/ር አብይ ይህንን የፈጣሪ ስም ሲጠሩ፤ እንደ ቀድሞ የእግዚአብሔርን ስም ይጠሩ እንደነበሩ ንጉሦች የመንግስትን ንግሥና ለማስቀጠል ሳይሆን፤ ሕዝቡ ንጉሥ የሚሆንበት አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንድትወለድ፤ አዋላጅ ባለስልጣን መሆንን ብቸኛ ተልዕኮዎ እንደሆነ መቁጠር ይገባዎታል። ለዚህም በሕዝብ ዘንድ እንደ ስጦታ እየተቆጠሩ እንደሆነ የኢትዮጵያ ልጅ የሆኑት ዶ/ር አብይ አህመድ እርስዎም የሚያውቁት ይመስለኛል። የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ተፎካካሪ ብለው እንደጠሩ ተሰምቶ ደስ አለን። ግን እነዚህን ፓርቲዎች ተፎካካሪ ስለተባሉ እውነትም ተፎካካሪ ሊሆኑ አይችሉም። የዲሞክራሲ ምህዳሩ ከሌለ አማራጭ ሃይል ለመሆን በአሳብ ዙሪያ ለመሰብሰብ አይችሉም። ያላቸው ምርጫ ዲሞክራሲ እስኪወለድ ድረስ መቃወም ነው። ስለዚህ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሆኑ፤ በመጀመሪያ ዲሞክራሲን የሚያዋልዱ አዋላጅ ለመሆን ቆርጠው መነሳት ይኖርብዎታል። አዲሲቷ ኢትዮጵያ የምትወለደው ልጆቿ ሁሉ ሲሳተፉ ስለሆነ፥ በመጀመሪያ ዲሞክራሲ መወለድ አለበት። ያኔ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተባባሪ አዋላጅ ሆነው ይገለጣሉ። በመጨረሻም አዲሲቷ ኢትዮጵያ በሕዝቧ ንጉሥነት ትወለዳለች። በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ ወደ ፈጣሪ እጆቿን ለመዘርጋት የምርጫ ነፃነት ይኖራታል። እስከ አሁን ግን ለዘመናት የንጉሣውያን መንግስታት እስረኛ እንደሆነች አለች። የኢትዮጵያ ሕዝብ ንጉሥ የመሆን ዕድል ካገኘ፤ ፈጣሪን የምድራችን ንጉስ እንደሆነ ዕውቅናን በደስታ እንደሚሰጥ የሚያውቅ የኢትዮጵያ አምላክ፥ እስካሁን ኢትዮጵያን ከጥፋት እየጠበቀ ዛሬ ደረስን። ዘረኝነት ከፋፍሎን እንዳያጠፋን ስጋት ውስጥ ገብተን ነበር። ዛሬ ፍቅር አሸንፎ በአንድ ልብ እንደ አንድ ቤተሰብ ለመሆን እየተሰራንና እየተያያዝን ያለንበት ወቅት ነው። የሁሉም ነገር ማሰሪያ ፍቅር እንዲሆን እያደረግን፤ ምድራችን በዲሞክራሲ፥ በፍትህ፥ በመልካም አስተዳደርና በልማት እንድትመነጠቅ ሁላችንም ለበጎ ስራ ተግተን አዲስ ታሪክ ይሰራ። ዶ/ር አብይ አህመድ ይህንን ታላቅ ተልዕኮ እንዲወጡ፤ ሁላችንም ወደ ፈጣሪ እሳቸውን በፀሎትና በምልጃ የምናቀርብበት ጊዜ ነው። ኢትዮጵያ በምጥ ላይ ነችና ሁላችንም አብረን በምጥ ሆነን ወደ ፈጣሪ እንቃትት ዘንድ ይገባል። ትልቁ የፈጣሪ በረከት ለዚህ ሁሉ ተልዕኮ መሠረት የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ቤተሰብነት ወደ ብርሃን ማምጣት ነው። ይህንንም በተመለከተ አንድ ነገር ልበልና ልቋጭ፦ አሜሪካኖች ስለ አሜሪካ “One Nation Under God” (በአምላክ ስር ያለ አንድ ሕዝብ) ይላሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ “One Family Under God” (በፈጣሪ ስር ያለ አንድ ቤተሰብ) ይሁንልን! እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርካታልም ኢሜል ethioStudy@gmail.com ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
ቃሉ የሕዝብ ነው። ቃሉንም በተግባር የሚተረጉመው ሕዝብ ነው። የወንዝ ውሃ ሽቅብ እንደማይፈስ ሁሉ፥ ይህም ቃል ወደ ተግባር ሳይቀየር ይቀለበሳል ብሎ መጠበቅ ተገቢ አይደለም። ይልቁንስ ይህን ቃል ለመተግበር የዶ/ር አብይ ድርሻ ምንድነው ብሎ አውቆ በዚያው ሚዛን ብቻ እርሳቸውን መመዘን ያስፈልገናል። ለሕዝብ ታማኝ ባይሆኑ፥ እሳቸው ከታሪካዊነት ይጎድላሉ እንጂ የሕዝብ ቃል ዕውን መሆኑ አይቀሬ ነው። ዶ/ር አብይ አህመድ የሚናገሩት ቃል እርሳቸው የፈለሰፉት ስለሆነ አይደለም የተወደደው። ቃሉ የሕዝብ ቃል ስለሆነ ነው እንጂ። ይህ ሰሚ ያጣ ሕዝብ በትግሉ የራሱን ቃል የሚያስተጋባ ጠ/ሚ ሊያመጣ ቻለ። ታዲያ ይህን ቃል የዶ/ር አብይ የግል ንብረት ተደርጎ፥ ቃል ዋጋ የለውም ብሎ ቃሉን ማጣጣል ለኢትዮጵያ አይጠቅምም። የውልጃ አብሳሪ የሆነ ቃል በውልደት ቀን ዋዜማ ሲሰማ፥ በተስፋና በትጋት ይህን የሕዝብ ቃል በክብር መያዝ ይገባል። ይህ ታላቅና አስገራሚ ሕዝብ ቃሉን በአደባባይ ካሳወጀ በሁዋላ፥ ይህ ቃል አይተገበርም ማለት የቃልን ምንነትና የቃሉ ነፀብራቅ የሆነውን ሕዝብ ማንነት ያለማወቅ ነው። ከአሁን በሁዋላ በምድራችን የሚሆነውን ነገር ለማወቅ ከተፈለገ ወደ ፊት በማየት ማገናዘብ እንጂ ወዳለፈው ታሪካችን እየተመለከትን ሽንፈትን ማስተናገድ አይበጅም። በመጀመሪያ ቃል ተወለደ። ይህ ቃል ቀጥሎ ዲሞክራሲን ይወልዳል። ዲሞክራሲ ሁሉን የኢትዮጵያ ልጆችን አሳትፎ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ያስወልዳል። ስለዚህ ይህ የታወጀው ቃል የምጥ መጀመሪያ ነው። ያለፈውን የእርግዝና ወቅት ሳይሆን አሁን ያለውን አዲስ የምጥ ሂደት ማስተናገድ ይገባናል። መወለድን ማስተጓጎል ቀርቶ ማዘግየት የሚቻልበት ወቅት ላይ አይደለንም። እናስተውል። አሁን ቸኩለን ስለ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ማውራትና መጠየቅ አንችልም። አሁን ዶ/ር አብይን በቅድሚያ የዲሞክራሲ አዋላጅነታቸውን ግዴታ እንዲወጡ ብቻ በተጠያቂነት መያዝ ይኖርብናል። ከዚያ ዲሞክራሲ ተቃዋሚ የሆኑትን ሃይላት ወደ አማራጭ ሃይልነት ቀይሮ ተባባሪ አዋላጅ ያደርጋቸዋል። ያኔ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብን ያሳተፈ ሂደት አዲሲቷን ኢትዮጵያ እንድትወለድ መቻልን ያመጣል። ሁሉንም የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚዳኝ ሕዝብ ነው። ለዚያ ዲሞክራሲ የመጀመሪያው መሰረት ነው። ስለዚህ ይህን የሕዝብ ቃል ይዘን ዲሞክራሲ በቅድሚያ ይወለድ ዘንድ ግድ እንበል። ኢትዮጵያን በጎሰኝነት ከፋፍሎ ሊበትን ጠላት ያቀደው በቃል ነበር። ፈጣሪ ኢትዮጵያን ወደሚጠብቃት ታላቅ ክብርና ሞዴልነት የሚወስዳትን ጉዞ የሚያስጀምረውም በቃል ነው። የአዋላጅነት ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ዘብ መቆም እኛም ከአዋላጆቹ ጎራ እንድንመደብ ያደርገናል። ዶ/ር አብይን በብዙ ጉዳይ እያዋከብናቸው እና አፍራሽ ቃል በመጠቀም ጥሪያቸውን እንዳይወጡ ለጠላት መጠቀሚያ እንዳንሆን እንወቅበት። በዶ/ር አብይ አዋላጅነት ሊሆን ያለውን ድል እንቅፋት እንዳንሆን መጠንቀቅ እጅግ ያስፈልገናል። ይህን የኢትዮጵያ ልጅ ለመውቀስም ሆነ ለማሞገስ አንዱንና ብቸኛውን ዲሞክራሲ ላይ ትኩረት በማድረግ መሞገትና ተጠያቂ ማድረግ መልካም ነው። ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ! ኢሜል ethioStudy@gmail.com ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
በጃንሆይ ዘመነ መንግስት ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ፋታ ስጡኝ እያሉ ቢጣሩም፥ ሰሚ አጥተው አቶ ጥድፊያ ኢትዮጵያን ላለፉት ዓመታት ለመከራ አሳልፎ እንደሰጣት እናውቃለን። ከታሪክ ጠባሳ ካልተማርን ታሪክ ራሱን ይደግማል። ለዶ/ር አብይ አህመድ ፋታ እንዲሰጥ የሚያስፈልገው ለእርሳቸው ስልጣን ማራዘሚያ አይደለም። ፋታ የምትፈልገው ኢትዮጵያ ናት። አሁንም ዶ/ር አብይን የሚያዋክቡ ወገኖቻችን ዓይናቸውን ከእሳቸው ላይ አንስተው እናት ሀገር የምትባለው ኢትዮጵያ ያለችበትን ምጥ ማየት ቢችሉ መልካም ነው። ጊዜው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለመወለድ ጫፍ ላይ ያለችበት ወቅት ይሆን ይሆንን? በማለት የአዋላጅነት ሚና እንድንጫወት ሁላችንም መጣር ያለብን ወቅት ነው። ከጥንቃቄ አንጉደል። ዶ/ር አብይ የሕዝብን ድምፅ አድምጠው፥ ይህንንም የሕዝብ ድምፅ ገንዘብ በማድረግ ከሌሎች ጋር ተቀናጅተው በሕዝብ ትግል እየተደገፉ እዚህ ደርሰዋል። በዚህም ምክንያት መላውን ሕዝብ ያስደመመና ከተዐምር የማያንስ ጉዳይ የሆነውን ኢትዮጵያዊነትን ሞሽረውና ሸልመው ሲያበቁ፥ ኢትዮጵያዊነትን ከወደቀችበት ጓዳ አውጥተው ብርሃኗ እንዲፈነጥቅ አድርገዋል። ለውስጥም ሆነ ለውጭ ተፎካካሪ አካላት የፍቅር ጥሪ በማድረግ ብዙ ተስፋ የሰነቀ ንግግር ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በማስረገጥ አሳውቀዋል። እርቅና መግባባት በምድራችን ዕውቅና ያገኘበትም ወቅት ነው። ሙያ በልብ ነው የሚለውን መርህ ያነገቡ የሚመስሉትን እኚህን የኢትዮጵያ ልጅ ማስተዋልን በተፋታ መልኩ ጥላሸት እየቀቡ መሞገት አሁን ጊዜው ነውን? “ሰሚ ያጣ ሕዝብ” በሚል ርዕስ የዛሬ ሁለት ዓመት (2016) ለንባብ ካበቃውት ፅሁፍ ልጥቀስ፦ “ከእንግዲህ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የለም። ማንም ላይታመን፥ ሕዝቡ ራሱን ብቻ ሊያምን ተነስቷል። ስልጣን የሕዝብ ነው እያሉ በስሙ የሚነግዱ ከእንግዲህ በቃችሁ ተብለዋል። ስልጣን የሕዝብ መሆኑን የሚናገር ሳይሆን በሕዝቡ ለመመራት ራሱን የሕዝቡ ተከታይ የሚያደርግ ብቻ ይፈለጋል። ከትልቅ ትዕግስት በሁዋላ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሕዝቡ የተነሳው፥ ለመንግስት ስልጣኑን የሚያስረዝምበትን መላ ለማፈላለግ፥ ወይም ለተቃዋሚ የስልጣን ውርስ እንዲያደርጉ ለማመቻቸት ሳይሆን፤ መሪዎቻችን የሕዝቡን ድምፅ እንዲሰሙ እና ስልጣንን ለባለቤቱ (ሕዝብ) ማስረከቢያውን መንገድ እንዲፈጥሩ ነው። ፈሪሃ ፈጣሪ ያለው ይህ ሕዝብ አምላክ እንዳለለት ይታወቅለት።” ከዶ/ር አብይ የቁርጠኝነት ቃል በመነሳት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰሚ አግኝቼ ይሆንን? እያለ በተግባር ለማየት በተጠንቀቅ በሚጠብቅበት በዚህ ወቅት፥ አፍራሽ የሆነ ነገር መናገርና ማደናገር ለማን ይጠቅማል? ይልቁንስ እነዚህ ትዕግት የጎደላቸው ወገኖቻችን የትግላቸውን ስልት ጊዜውን እንዲመጥን በማደስና ከሕዝብ የልብ ትርታ ጋር በማጣጣም ፋታ ለኢትዮጵያ ቢሰጡ አይበጅምን? የሩስያው ፕሬዚዳንት ጎርቫቾቭና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሬገን “እመን ግን አረጋግጥ” እያሉ ታሪክ ሰሩ። ይህንን መርህ በመጠቀም ትግሉን በቀና መንፈስ አጠናክሮ ገንቢ በሆነ አካሄድ መንቀሳቀስ ማስተዋል ነው። ለሁላችንም ልቦና ይስጠን። ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ! ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
የተወደዱ ዶ/ር አብይ አህመድ እፎይ የሚያሰኝ ቃላቸውን አሰምተውን ሳለ፥ እኛ ግን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተነስተን ስጋት ውስጥ መግባታችን የሚታይ ጉዳይ ነው። ክቡር ዶ/ር አብይ ሕገ መንግስቱ የሚፈቅድላቸውን ስልጣን በሙላት እንዳይጠቀሙ እንቅፋት ሊኖርባቸው ይችላል እየተባለ ስጋት ውስጥ መገባቱ አግባብ ሊሆንም ይችል ይሆናል። ራዕይን የሰነቀ ንግግራቸውን የሚተች ሆነ ስብዕናቸውን የሚጠራጠር እምብዛም አይታይም። የሁሉም ጥያቄ ያሰሯቸው ይሆንን የሚለው ስጋት ነው። ከዚህ በፊት “ዘብ ቆመናል ክቡር የኢትዮጵያ ልጅ ዶ/ር አብይ አህመድ” በሚለው ፅሁፌ እንደገለፅኩት፥ ዶ/ር አብይ አህመድ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለኢሕአዴግም ጭምር በረከት ናቸው። ክቡር ዶ/ር አብይ ለኢሕአዴግ ከተጋረጠበት አጣብቂኝ መውጫ ቀዳዳና እንዲሁም ኢሕአዴግ ለሚቀጥለው ምርጫ በሕዝብ በእውነተኛ ምርጫ ሊያሸንፍ በሚችልበት በሚመስል መልኩ ዕድልን ያገኘ ነው። ያም ሆኖ ዶ/ር አብይ አሕመድ ህዝብን ያስደመመውን የሕዝብ የልብ ትርታ ነፀብራቅ የሆነውን ንግግራቸውን በስራ ለመግለፅ ፈተና አለባቸው ከሚል ስጋት ለመላቀቅ የተቻለ አይመስልም። የተወደዱ ዶ/ር አብይ አህመድ ያላቸውን አቅም ከምንም እንደሚበልጥ የተረዳነው አይመስለኝም። ያም አቅም ምንጩ የሕዝብ ፍቅርና አመኔታ ነው። ይህንን የሕዝብ ፍቅርና አመኔታ ወደ ትልቅ አቅም በመቀየር ፈተናቸውን ለመወጣት የሚችሉት ራሳቸው ዶ/ር አብይ በሚያደርጉት ድርጊት ነው። ፈተናቸውን በድል ለመወጣት አቅም እንዲኖራቸውና ለሕዝብ ቃል የገቡትን በስራ ለመተርጎም የሚያስችላቸው ቁልፍ በራሳቸው እጅ ነው ያለው። ስለዚህ መስጋት ካስፈለገን ዶ/ር አብይ የሚታመኑ አይደለም በማለት እንጨነቅ እንጂ አቅም አይኖራቸው ይሆናል ብለን አንፍራ። ዶ/ር አብይ አህመድ አዋላጅ ባለስልጣን ናቸው። አዋላጅ መንግስት ከማየታችን በፊት አዋላጅ ባለስልጣናት መገኘት አለባቸው። አዋላጅ መንግስት ራዕዩ ራሱን ከንጉስ መንግስትነት አላቆ ሕዝብን ማንገስ ነው። ያኔ ንጉስ የሚሆነው ሕዝብ አገልጋይ የሚሆንለትን መንግስት መምረጥ እንዲችል መድረኩ ያመቸ ይሆናል። አሁን ያንን አዋላጅ መንግስት ዕውን ለማድረግ አዋላጅ ባለስልጣን የሆኑት ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ ባለ አደራ ናቸው። አዋላጅ ባለስልጣን መሆን በክቡር ዶ/ር አብይ ተጀምሮ በክቡር ዶ/ር አብይ የሚደመደም አይደለም። ክቡር አቶ ለማ ሀገርን ከስልጣን አስበልጠው ዶ/ር አብይን ማስቀደማቸው አዋላጅ ባለስልጣን ያደርጋቸዋል። ክቡር አቶ ደመቀ ለራሳቸው ስልጣን ከማቀንቀን ይልቅ ራሳቸውን አግልለው ዶ/ር አብይን ማስቀደማቸው አዋላጅ ባለስልጣን ያደርጋቸዋል። እንደዚሁም ክቡር አቶ ሃይለማርያም ስልጣናቸውን ለቀው ለዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት ምክንያት መሆናቸው አዋላጅ ባለስልጣን ያደርጋቸዋል። እነዚህን ለምሳሌነት ጠራው እንጂ እንደ እነ ክቡር አቶ ገዱ የመሳሰሉና ለመመረጥ ያበቋቸው ከመቶ በላይ የሆኑት የኢሕአዴግ አመራሮች እየተቀባበሉ ዶ/ር አብይን ወደ ስልጣን አምጥተዋል። እንደኔ ክቡር ዶ/ር አብይ ያደረጉት ንግግር ከምንም በላይ ባለስልጣኑ ሕዝብ እንዲሆን የሚፈልጉና ሀገርን ከራሳቸውና ከሁሉ በላይ እንዳስቀደሙ ያሳያል። ስለዚህም ዶ/ር አብይ ከስልጣናቸው ጋር የሚጣበቁ ሰው እንደማይሆኑ ግልፅ ነው። በብዙ አዋላጅ ባለስልጣናት መስዋዕትነት ታጅበውና የሕዝብን ፍቅርና አመኔታ ተገን አድርገው ለስልጣን ከመሳሳት ይልቅ ለሕዝብ ለማደር ምንም እንደማይቸገሩ መገመት ከባድ አይደለም። ታዲያ ይህን ሁሉ ከቁጥር ስናስገባ ክቡር ዶ/ር አብይ ከምንምና ከማንም በላይ ራዕይን የሰነቀውን ንግግራቸውን በተግባር ለመፈፀም አቅም አላቸው ማለት እንችላለን። ምክንያቱም እውነትን ይዘውና የሕዝብን ምኞት አንግበው፥ በሕዝብ ልብ ውስጥ ገብተው በሕዝብ ከለላ ተጠልለዋልና ነው። ስለዚህም ሲሆን ሲሆን ከቻሉ ይህንን የሚወዳቸውን ሕዝብ ማገልገል፥ ካልሆነ ደግሞ ስልጣናቸውን አሽቀንጥረው ለመጣል ብቃት ያላቸው ይመስለኛል። ምንም እንኳን ሕዝብ ባይመርጣቸውም፥ በመመረጣቸው ሕዝብ መደሰቱና ምርጫቸውን ማፅናቱ በእሳቸው ልብ ውስጥ የሚፈጥረውን የባለ አደራ ቁርጠኝነት መገመት ይቻላል። ከዚህም የተነሳ እሳቸው በስልጣን እያንዳንዷን ቀን ማሳለፍ የሚፈልጉት ይህንን ሕዝብ ለማገልገል እስከቻሉ ድረስ ብቻ ይመስለኛል። ስለዚህ ጊዜው የትጋት እንጂ የስጋት መሆን የለበትም። በእርግጥ እሳቸውን አላሰራ የሚል ቢሮክራሲ ተደቅኖባቸው ሕዝብን ማገልገል ካልቻሉና በዚህም ምክንያት ስልጣናቸውን ከለቀቁ ያኔ መስጋት ያስኬዳል። ይህንን እንደ ባለ አዕምሮ ሰው ካልኩኝ፥ ደግሞ እንደ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እምነት አንድ ነገር ልጨምር። ባብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈጣሪውን እየተማፀነ፥ የኢትዮጵያም አምላክ ኢትዮጵያን እየጠበቀ እዚህ እንደተደረሰ የአደባባይ ምስጢር ነው። በአንድ ቀን ጀንበር የተወደዱ ክቡር ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከተደበቀበት ጓዳ አውጥተው ከፍ አድርገው ሲያሳዩን፥ ሁላችንም በኢትዮጵያዊነታችን ኮርተንና ተደንቀን እጅ ለእጅ በፍቅር ለመያያዝ በቃን። ታዲያ ይህን ሁሉ ከተዐምር ያላነሰ ድርጊት ስናይ፥ የአምላክ እጅ አለበት ብለን ለማመን ለብዙዎቻችን አይቸግረንም። የኢትዮጵያን ትንሳዔ በማብሰር የጀመረው ፈጣሪ፥ አዲሲቷ ኢትዮጵያ እስክትወለድ ድረስ ለጠላቷ ዕድል እንደማይሰጥ በማመን ከስጋት ወደ ትጋት ተሻግረን ሁላችንም የአዋላጅነትን ሚና ለመጫወት ነገ ሳይሆን ዛሬ እንነሳ። ኢትዮጵያ ትንሳዔን አግኝታለችና ከእንግዲህ ሕዝቧ ሰሚ ያጣ ሕዝብ ተብሎ መጠራቱ ያከትማል። የማታ የማታ ሰሚ ያገኘች ይህች እናት ሀገር፥ ማንም ይሁን ምንም ይህንን የኢትዮጵያ ትንሳዔ ሊቋቋም የሚችል ሃይል ከሰማይ በታች ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም ከሰማይ በላይ ያለው ፈጣሪ በቃ ያላት ወቅት ነውና። ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ! ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
ሁላችንም ካለንበት አጣብቂኝ ውስጥ መውጫ መንገድ አጥተን ተፋጠን ሰንብተናል። ስንነካከስ እንዳንጠፋፋ በሚያስፈራበት መልኩ ሁላችንም ግብ ግብ ስንገጥም እዚህ ደረስን። መንግስት በጉልበቱ ሲገፋበት፥ ሕዝብ በአመፁ ሲዘልቅበት፥ አማራጭ ኃይል በሁሉ አቀፍ ትግሉ ሲዘምትበት፥ አካሄዱ ሁሉ ሲያስፈራ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን ያሰኝ ነበር። ሕዝቡ ሁሉ በሁሉም አቅጣጫ ወደ አምላኩ ከመጮህ አልተቆጠበም። በአራቱም አቅጣጫ አንድነቷን እና ብልጽግናዋን በማይወዱ የተከበበች ሀገር ሆና ሳለ፥ ከውስጥ ደግሞ በነውጥ ስትናጥ ተስፋዋ እየመነመነ ጫፍ ደርሶ ነበር። ምን አልባት ታዲያ የማታ ማታ ፈጣሪዋ ኢትዮጵያን ከምጥ ሊገላግላት፣ ውጥረቷን አርግቦ ሰላምን ሊሰጣት አስቦ ይሆን ዶ/ር አብይ እርስዎን ወደ አመራር ያመጣዎት? ካለንበት አጣብቂኝ ለመውጣት ረዥም መንገድ መሄድ እንዳለብን እሙን ነው። ዶ/ር አብይ ለኢትዮጵያ ዘብ በመቆምና እኛም ለእርሳቸው ዘብ በመቆም ይህን የተስፋ ጭላንጭል ጠላት እንዳያጨናግፍ ሁላችንም የየበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይገባናል። አሁን ከፊታችን የተደቀነው ወሳኝ ሰዓት እኛ ተመልካች ሆነን፥ ዶ/ር አብይ ደግሞ በፊታቸው ያለውን ፈተና ያልፉ እንደሆነ ለማየትና ብያኔ ለመስጠት በጥርጥር ዓይን የምንመለከታቸው አይደለም። ወይንም እኛ ሁላችን እሳቸውን የምናዋክብበት ጊዜ አይደለም፤ ነገር ግን እኛም ሆንን እሳቸው የመፍትሄው አካል ከመሆን እንዳንጎድል የምንጠነቀቅበት ጊዜ ከምን ጊዜውም በላይ አሁን ነው። በአንደኛ ደረጃ፥ ህዝብ ካንዣበበት አደጋ አምልጦ በሰላምና በመረጋጋት እንዲኖር ዶ/ር አብይ ራስዎን ከአጣብቂኝ መውጫ አድርገው ለሕዝብ የተሰጡ ይሆኑ ዘንድ የተሰጠዎትን የሕዝብ ፍቅርና አመኔታ አነሳስተዎት ለኢትዮጵያ ዘብ ይቆማሉ ብዬ አምናለሁ። ከዚህ በፊት በተለያዩ መድረኮች ያደርጉ የነበረውን ንግግርዎትንና ስብዕናዎን፣ አምላክ ወደ ብርሃን አውጥቶ በሕዝቡ ልብ ውስጥ እርስዎን አስቀምጧል። ሕዝቡ ትልቅ ተስፋም እንዲኖረው አድርጓል። እርስዎ ታማኝነትዎን ለመንግስት ዕድሜ ቅጠላ ሳይሆን ሰሚ ላጣው ሕዝብ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው። ለጠ/ሚ ስልጣንም ያበቃዎት በቀዳሚነት የሕዝብ ትግል ነውና። በመንግስት ዘንድ የሕዝብ ጆሮና ዓይን በመሆን የሕዝብ ጠበቃ እንዲሆኑና የሚመሩትን መንግስት ወደ አዲሲቷ ኢትዮጵያ አዋላጅነት እንዲያሻግሩ ታሪካዊ ጥሪያዎን ይወጡ ዘንድ ተልዕኮዎን ለአንዲትም ደቂቃ መዘንጋት የለብዎትም። ይህንንም ሃላፊነትዎን እንዲወጡ ፋታ ባገኘሁ ይሉ ይሆናል። ግን ፋታ እንዲሰጥዎት የሚያደርጉት እርስዎ ራስዎ በሚያደርጉት ተግባር ነው። በማስተዋል በመመላለስ ሁለት ነገሮችን ቢያደርጉ ፋታ የሚያገኙ ይመስለኛል። በመጀመሪያ የሕዝብን ጥያቄ በየደረጃው ለመመለስ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ መንቀሳቀስን ቸል የማይሉት ነገር ሆኖ ሲገኝ ነው። በሁለተኛ ደረጃ የምንሄድበትን አዲስ አቅጣጫና ራዕይ እየነገሩንና አድራሻችንን እያሳዩን፥ አንድ ልብ ኖሮን እንደ አንድ ቤተሰብ የምንሄድበትን አካሄድ ለማስጨበጥ የሚተጉ ሆነው ሲገኙ ነው። አባቶች ደማቸውን አፍሰው በመሞት ኢትዮጵያን አቆይተው ዛሬ ለዚህች እናት ኢትዮጵያ ጠ/ሚ ለመሆን ታድለዋል። በተራዎ እርስዎ ራስዎ ለኢትዮጵያ በመኖር ኢትዮጵያን የሁሉ በእኩልነት የመኖሪያ እና የማረፊያ ሀገር እንድትሆን የበኩሉዎን ታሪካዊ ድርሻ መወጣት ይጠበቅብዎታል። ሁሉም መልካም ምኞቱንና በጎ ፍቃዱን እንደለገሰዎት በማወቅ ለተሰጠዎት ለዚህ ታላቅ ፀጋ ታማኝ እንዲሆኑ ማስተዋል ይብዛልዎት። በሁሉ ነገር መልካም እንዲሆንልዎት የመላው ኢትዮጵያዊ ፀሎትና ሰላማዊ ትግል እንደማይለይዎት ጽኑ እምነቴ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፥ ኢሕአዴግ ራሱን ለማትረፍ ከዶ/ር አብይ የበለጠ መውጫ አያገኝምና ለዶ/ር አብይ ዘብ በመቆም ህልውናውን በሀቅ ምርጫ ለማስቀጠል ራሱን ካለው የጊዜው የሕዝብ ጥያቄ ጋር ማጣጣም ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በቅንነት አገልጋይ ለሆነ ሁሉ የሃይማኖት የጎሳና የፖለቲካ ፓርቲ አባልነቱ ማንነት ውሳኔውን ሳያዛባ በአስተሳሰቡ ምንነት ላይ ብቻ ተደግፎ ፍቅሩን እንደሚለግስ በዶ/ር አብይ ምርጫ ምክንያት የታየው ደስታ ያረጋግጣል። ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብን ቅንነትና ታላቅ ስብዕና ያሳያል። እስካሁን መንግስት የሄደበት አካሄድ ስልጣንን በጉልበት እንጂ በእውነተኛ ምርጫ አላገኝም ብሎ ያመነ ይመስል ከዲሞክራሲ የተፋታ ነበር። ታዲያ ዛሬ በእነ ክቡር አቶ ለማና ክቡር አቶ ገዱ ሕዝብን የማዳመጥና የማገልገል አስተሳሰብ ራሱን አጥምቆ ቢንቀሳቀስ፥ በእውነተኛ ምርጫ ለስልጣን የመታደል ዕድል ሊያገኝ እንደሚችል ጭላንጭል እየታየ ነው። የትኛውም በጦር የመጣ መንግስት እኔ እስከማውቀው ድረስ እንዲህ ያለ የመሸጋገሪያ ድልድይ ከራሱ አብራክ በወጣው ልጅ ዕድል ሲያገኝ አላየሁም ደግሞም አልሰማሁም። በጎም ሆነ ክፉ እያደረገ ለ27 ዓመታት እንደፈለገው ገዝቶ ሲያበቃ፥ እንደገና በዲሞክራሲ በመዳኘት በምርጫ ስልጣኑን ቢያጣ እንኳን እንደ ኢሕአዴግ ህልውናውን ከመጥፋት አስመልጦ ማስቀጠል የሚችልበትን ዕድል አግኝቷል። ታዲያ ለዚህ ምክንያት የሆኑት ዶ/ር አብይን በሙሉ ስልጣን የመመራት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላት በመረባረብ የውስጥ እንቅፋት የሚሆነውን ሁሉ በማሳመን ሕዝብን ማክበር ይኖርባቸዋል። በሦስተኛ ደረጃ፥ ተቃዋሚው ሃይል ለኢትዮጵያ አማራጭ ሃይል ለመሆን ዶ/ር አብይ ሁነኛ መውጫ ሊሆኑ ብቃት ያላቸው ይመስላሉና ለዶ/ር አብይ ዘብ በመቆም ለሰላሙ ትግል ሃይሉን አጠናክሮና አቀናጅቶ መቅረብ ይኖርበታል። ተቃዋሚው እውነተኛ ምርጫ እንዲዳኘው የሚያስችል የዲሞክራሲ ምህዳር ቢኖርለት የአመፅ ናፍቆት የለውም። የዲሞክራሲው ምህዳር እንዲሰፋና እንዲንሰራፋ መድረኩ ክፍት ከሆነ፥ በውጭም ሆነ በውስጥ ያሉት ተቃዋሚዎች አማራጭ ሃይል ለመሆንም ሆነ ለመተባበር ዕድል ፈንታ ይሰጣቸዋል። ለዚህም ነው ተቃዋሚ ሃይሎች ዶ/ር አብይን ለዲሞክራሲ ጉዞ ከአጣብቂኝ መውጫ ይሆኑ ዘንድ ደጀን በመሆን እውነት ራሷ ይህንን የዲሞክራሲ አካሄድ የሚቃወሙትን እንድትሞግትና እንድትረታ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ይበልጥ መቀናጀት የሚያስፈልጋቸው። ለማንኛውም የዛሬ ሁለት ዓመት ሊመጣ ያለውን ምርጫ ከቁጥር በማስገባት እስከዚያው ድረስ ዶ/ር አብይ ለምርጫው ፍትሀዊነት ሁሉን እያሳተፉ የለውጥ ዋዜማ ሽታ እስካመጡ ድረስ በትዕግስትና በመረዳት ፋታ መስጠት የግድ ነው። አሁን ዶ/ር አብይን በተመለከተ በሁሉም አማራጭ ሃይሎች ዘንድ የሚታየው በጎ ፍቃድና የእምነት ተስፋ እጅግ የሚያበረታታቸው ይመስለኛል። ይህም መልሶ ለሕዝብ እንዲኖሩ ግፊት እያደረገ የሕዝብ እውነተኛ አገልጋይ እንዲሆኑ ጉልበት ይሆናቸዋል። ላለፉት 44 ዓመታት በወጀብ ስትናወጥ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ ደግሞ በአዲስ መንፈስ መሪዋና ሕዝቡ በፍቅር እጅና ጓንት ሆነው አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንድትወለድና ሀገራችንም ለመጀመሪያ ጊዜ እፎይ የምትልበት ዘመን ይህ ጊዜ ይሁንልን። ይህ መለኮታዊ ዕድል አያምልጠን። ልባችን ለዚህ ውልደት ዘብ ለመቆም ይጨክን! የኢትዮጵያ አምላክ ኢትዮጵያን አሰበ። ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ! ኢሜል፡ ethioStudy@gmail.com ከዶ/ር ዘላለም እሸቴ
ሰሚ ያጣ ሕዝብ ብዬ የፃፍኩት ትዝ ይለኛል። ጆሮ ያለው ይስማ ብዬ የፃፍኩትም የእርስዎን ምርጫ በመመኘት ነበር። ዛሬ ፓርቲዎ ኢሕአዴግ ሕዝብን የመስማት አገልግሎት ለመጀመር እርስዎን በጠ/ሚኒስቴርነት መሾሙ ድንቅ የሚያሰኝ ነው። ከጦረኛ መንግስትነት ወደ አዋላጅ መንግስትነት መሸጋገር የእርስዎ ብቸኛ ትኩረትዎ እንዲሆን ማስተዋል እንዲበዛልዎት እመኛለሁ። አብዮት ከመወለዱ በፊት ኢትዮጵያ እንደገና እንድትወለድና ሁላችንም በእኩልነት የምንኖርበትና በዲሞክራሲ የምንዳኝበት አዲሲቷን ኢትዮጵያ ዕውን በማድረግ መንግስትዎንና ሀገራችንን ከጉድ ለማትረፍ ጥሪዎን እንዲወጡ ፀሎቴ ነው። አዋላጅ መንግስት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከዚህ በታች ለማስረዳት እሞክራለሁ። እስካሁን በተሄደበት መንገድ በጦር የመጣ መንግስት ስልጣንን እንደ ክፍያውና ዋጋው አድርጎ ይወስዳል። “ማን በደማ ማን ይነግሳል?” ይላል። በእርስዎ አመራር መንግስትዎ አዋላጅ መንግስት ሆኖ፥ ይህ አዋላጅ መንግስት በጦር የመጣው ለመንገስ ሳይሆን፥ ደም ዳግም ለዘላለም እንዳይፈስ ምርጫን በሀቅ ወዶ ሕዝብን ለማንገስ እንዲሆን እርስዎ መንገድ እንዲሆኑ በተስፋ ይጠበቃሉ። ይህች የመጨረሻዋ ሰዐት ናትና የኢትዮጵያ አምላክ ታላቅ የታሪክ ዕድል ባለ አደራ አድርጎዎታል። ኢትዮጵያ በሁሉ አደገች እየተባለ፤ ነገር ግን በዋናው ጉዳይ በዲሞክራሲ ወደ ቁልቁል ተንደርድራ ስትሄድ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች። የኢትዮጵያ አዋላጅ መንግስት ምኞት በዋነኝነት ስልጣንን በምርጫ እስከ ማስረከብ የተዘጋጀ መሆን አለበት። ለዚህም መገለጫ የመንግስት ጤንነት ልብ ትርታ የሚለካው በተዘረጋው የዲሞክራሲ ባህልና እሴት እድገት ነው። ቀን ባለፈ ቁጥር ይህ መንግስት አዋላጅ የመሆን ዕድሉን እያጣ ይሄዳል። ዕድሉን በአብዩት ይነጥቅና ለሌላው ደግሞ ያስረክበዋል። አብዮት ደግሞ እሳት ነውና በጥፋት ውስጥ አሳልፎ ሕልማችንን ያዘገየዋል። ተስፋችንንም ያጨነግፈዋል። ታሪክና አጋጣሚ የኢትዮጵያ አዋላጅ መንግስት ለመሆን የሚያድለው ለአንድ መንግስት ብቻ ነው። ይህ መንግስት በእርስዎ መሪነት አዋላጅ መንግስት ለመሆን ጊዜው የሰጠውን ዕድል ይጠቀምበት ይሆን? እንቢ ብሎ ራዕዩ ለራሱ ስልጣን ባለቤትነት ከሆነ ያው አምባገነንነትን የሙጥኝ ብሎ በተራው እስኪወድቅ ድረስ መንገታገት ይችላል። ግብ ግብ እየገጠመና በፊቱ ያለውን እየገደለና እያሰረ ዕድሜውን ትንሽ ያስረዝም ይሆናል። ይሁን እንጂ በጠብ መንጃ ዕድሜ ልክ መግዛት አይቻልምና ስፍራውን ሲለቅ ያኔ አዋላጅ መንግስት የመሆኑን ዕድል ለሚቀጥለው አስረክቦ በራሱ ላይና በሀገር የታሪክ ጠባሳ ጥሎ ይቀራል። ነገር ግን የአዋላጅ መንግስት ራዕይ በአንደኛ ደረጃ አገር ማልማት ብቻ አይደለም። ሀገር ማልማት በሁለተኛ ደረጃ መያዝ ያለበት ራዕይ ነው። የአዋላጅ መንግስት የአንደኛ ደረጃ ተልዕኮ ስልጣንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሕዝብ ማዛወርና ጊዜው ሲሞላ በክብር ዘወር ማለት ነው። ምንም በሕዝብ በእውነተኛነት ቢመረጥ እንኳን የአዋላጅነትን ክብር የሚጎናፀፈው ጊዜው ደርሶ በምርጫ ሲሰናበት ነው። አምባገነን መንግስት ስልጣኑን ለማራዘም ድንጋይ ይፈነቅላል። አዋላጅ መንግስት ግን እውነተኛ ምርጫ እንዲዳኝ ይናፍቃል። ታሪክን ጨብጦ ስልጣኑን መልቀቅ ራዕይው ነው። አንድ ቀን በሌላ ተመራጭ እንደሚተካ በመገንዘብ ሌላውን በክብርና በቅንነት ያስተናግዳል። እርሱ ራሱ ታሪክ እንዲሰራ አማራጭ ሃይሎች ታሪክ እንዲሰሩ ይፈቅዳል። ምክንያቱም አዋላጅነት አብሮ በማሸነፍና በዚያም በኩል ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ማድረግን ይጠይቃልና። አዋላጅ መንግስት ተባባሪ አዋላጅ የሆነው አማራጭ ሃይል ያስፈልገዋል። በአገር ውስጥ ያሉትም ሆኑ በውጭ የሚኖሩት አማራጭ ሀይሎች ጭምር ለምርጫው ውድድር የሚያሳትፍ ጥሪ በማድረግ ሰላማዊው ጉዞ በአሸናፊነት ወደፊት እንዲራመድ ለማድረግ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ዲሞክራሲ አለ ማለት ብቻ ሳይሆን ዲሞክራሲ የሚተገበርበትን መድረክ አብሮ ማዘጋጀትና መስጠት ያስፈልጋል። ለሰላማዊ ትግል ሞራል የሚሰጥና የአመፅ ትግልን የሚያስጥል አካሄድ በመሄድ በፍጥነት መንቀሳቀስ ይበጃል እንጂ አስቸኳይ አዋጅ እያሉ ጊዜ መግደል ትንሽቷን ፋታ ያሳጣና በመጥፋትና በመጠፋፋት ኪሣራ ይደመደማል። እሳትን ማዳፈን እሳትን ማጥፋት አይደለምና። በዲሞክራሲ መንገድ ሄደን ስለማናውቅ የዲሞክራሲ ባህል እንዲዳብር አማራጭ ሃይልን የሚያሳትፍ መድረክ ከዛሬ ጀምሮ የሁልጊዜ ፕሮግራም መሆን አለበት። ቋሚ የሆነ ሃሳቦችን የሚያንሸራሽርና ሁሉም ጎራ ፕሮግራሙን የሚያስተዋውቅበትና ለሕዝብ የሚያደርስበት መድረክ ማበጀት የአዋላጅ መንግስት ትልቁ ስራው ነው። የመንግስትን ሚዲያዎች ለሁሉም ከፍቶ በእኩልነት የሁሉንም አሳብ በሕዝብ ፊት እንዲወያዩበት ማድረግ አለበት። የአምባገነን ትኩረት ሚዲያን ለራሱ ስልጣን ማጠናከሪያ የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ አድርጎ መጠቀም ነው። የአዋላጅ መንግስት ትኩረት ግን ሚዲያን ለመግባባት፥ለመማሪያ እና ለማስተማሪያ ማድረግ ነው። ከሁሉም በላይ ምርጫው በሁሉ ዘንድ ተዐማኒ እንዲሆን እንደ ምርጫ ቦርድና የመሳሰሉት ምርጫውን በተመለከቱ ነገሮች ላይ ሁሉ ሁሉም ተሳታፊዎችና ያገባኛል የሚሉ ሁሉ በእኩልነት ለፍትሀዊና እውነተኛ ምርጫ መሰረቱን ይጣሉ። አዋላጅ መንግስት ዓላማው ጊዜው ሲሞላ በምርጫ ተዳኝቶ ስልጣን ለቆ ታሪካዊ መሆን ነው። ስለዚህም የሚሄድበት አካሄድ ሕዝብን በመስማትና በማገልገል ነው። ምክንያቱም ባለስልጣን ሊያደርግ የሚፈልገው ሕዝብን ነውና። አዋላጅ መንግስት በሕዝብ በሐቅ መንገድ ቢመረጥ እንኳን ይህ ሆኖ መገኘቱ አሳብ ያስይዘዋል እንጂ አያስፈነጥዘውም። ምክንያቱም የአዋላጅ ሕልም ስልጣንን ለሕዝብ መስጠት እንዲታወቅለት ስልጣን ማስረከቡን ነው የሚናፍቀው። ለአዋላጅ መንግስት ኩራቱ በምርጫ ተሰናብቶ ኢትዮጵያን ማዋለድ ነው። እስከዚያው ድረስ መድረኩን ለነፃ ውይይት መልቀቅና ፍትሀዊ ምርጫ የሚደረገበትን አካሄድ ሁሉ በአሳታፊነትና በአብሮነት ከሚመለከተው ሁሉ ጋር መቅረፅ ዋነኛ ስራው መሆን አለበት። ይህ መንግስት ለዘላለም ለመግዛት ፈልጎ በአምባገነንነቱ ቢቀጥል ሊገዛ የሚችልበትን ዕድሜ አብዮት ያደናቅፈውና ዕድሜው እጅግ አጭር ይሆንበታል። ግን ይህ መንግስት አዋላጅ ለመሆን ፈልጎ በምርጫ ሰማዕትነትን አሳይቶ ኢትዮጵያን ለማስወለድ አንደኛ ዓላማው ቢሆን ሊገዛ የሚችልበት ዕድሜ ረጅም ሊሆንለት ይችላል። ምክንያቱም መንግስት ይህን የላቀ ራዕይ ይዞ ቢንቀሳቀስ፥ ከእርሱ የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ተቃዋሚው የበለጠ ስራ መስራት ስለሚኖርበት ነው። መንግስት ልቆ ከተገኘ፥ ሕዝብ ያለውን መንግስት ይመርጣልና ነው። መንግስትን የሚለውጠው የተሻለ አማራጭ እስካገኘ ድረስ ብቻ ነው። ስለዚህ ተቃዋሚው ስልጣን የሚያገኘው ራሱ በሚሰራው ስራ እንጂ መንግስት ባልሰራው ስራ ላይ የተመሰረተ አይሆንም። መንግስት በአምባገነንነቱ ከቀጠለ፥ ለዓመፅና ለጦር ቤንዚን እንደማንከርከፍ ይቆጠራል። እሳቱ አብዝቶ እንዲነድ አድርጎ ሲያበቃ ያንን ለማጥፋት ሃይሉን ቢጠቀም የማታ ማታ ቃጠሎው እርሱንም ይዞ ይሄዳል። ኢትዮጵያም ከዜሮ እንድትጀምር ትገደዳለች። ከዜሮ መጀመር ድሮ ተችሎ ይሆናል። ዛሬ ግን ከዜሮ ለመጀመር የሚደረገው ፉክክር አገሪቷን አደጋ ላይ ይጥላታል። በዜሮም እንድትቀር ያደርጋታል። ይህ መንግስት ግን አዋላጅ መሆንን ቢመርጥ የወደፊቱ መንግስት እርሱ በገነባው ላይ እንዲቀጥል ያደርጋል። ያኔ ከመንበረ ስልጣኑ እንኳን ቢለቅ ታሪኩና ስራው ለዘላለም ይኖራል። ያ ብቻ ሳይሆን ተመልሶ ወደ ስልጣን መጥቶም ሌላ የላቀ ምግባር ሊያከናውን በሩ ክፍት ይሆንለታል። ኢትዮጵያም ከዜሮ ከመጀመርና ሁሉንም ነገር በዜሮ ከማባዛት ትድናለች። አዋላጅ መንግስት ተቃዋሚዎች ሁሉ ከተቃዋሚነት ወደ አማራጭ ሃይላት ይዛወሩ ዘንድ ተስፋ ይሰጣል። ያኔ የአማራጭ ሃይላት ትኩረት አንድነት ይሆናል። አዋላጅ መንግስት ስልጣን ለመልቀቅ ሰማዕትነትን ሲናፍቅ፥ አማራጭ ሃይላት ደግሞ ሰማዕት ሆኖ የግል አጀንዳ ለቆ በአንድ ልብ ይቀናጃል። እውነት እንነጋገር ካልን፥ ጦረኛ መንግስት በራሱ ብቻውን ታሪክ ሰርቶ ሰማዕት ሆኖ ስልጣንን ለሕዝብ አስረክቦ በታሪክ ለመታወስ አይችልም። ኢትዮጵያ እንድትወለድ መንግስት ቀዳሚውን ሚና ቢጫወትም፥ የተቃዋሚዎችና የእያንዳንዳችንን አስተዋፅዎ ይፈልጋል። ተቃዋሚ ጦር ባይኖረውም ትልቁ ሃይሉ አንድነቱ ነው። ራሱን መስዋዕት የሚያደርገው የግልን ምኞትና አጀንዳ በመተው ለሀገር ሲባል በአንድነት መያያዝ ሲችል ነው። ይህ አዲስ አመለካከት የሚጠይቀው ያልተሄደበትን መንገድ መምረጥን ነው። ለዚህም እያንዳንዱ ተቃዋሚ ከራሱ ሩጫ ታቅቦና ከራሱ ማንነት ወጥቶ፥ ዓላማቸውንና ግባቸውን እንደገና በህብረት ሆነው ኢትዮጵያን ከማዋለድ ዓይን አንፃር ቀርፀውና አስተካከለው መነሳት ይኖርባቸዋል። ይህ ሲሆን መሪነቱን የጨበጠው ሁሉ የግሉን ለቆ የራሱን አውራነት ሰውቶ በአደጋ ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ ለመታደግ የአንድነት ፋና ወጊ ለመሆን መሽቀዳደም ይኖርበታል። ያለውን መንግስት በካርድ ምርጫ መቀየር እንዲቻል ራሳቸውን ማዘጋጀት ይገባቸዋል። ምንም ይሁን ምን ውልደት ምጥ ውስጥ ታልፎ ነው ሀሴት የሚበሰረው። ስለዚህም ነው የየግል አጀንዳቸውን ሰውተው ከተቃዋሚ ሃይሎችነት አንድ ወይ ሁለት ፈርጠም ያለ አማራጭ ሃይል መመስረት የሚገባው። ይህን የምንለውን አይነት አስተዳደር የሚመጥን ታላቅና ክቡር ነገር በምድራችን እንዲሆን ከተፈለገ የሁሉንም ሰማዕትነት ይጠይቃል። ያለውን መንግስት ስልጣን ልቀቅ ብሎ መሞገትና ሕዝብን ማነሳሳት ከራስ ጥቅም ያለፈ መሆኑ እንዲህ ካልተደረገ በምን ይታወቃል? የሚሞተው ሌላ፥ ሄዶ የሚነግሰው ሌላ እንዳይሆን ይሁን። የወጣቱ ደም ተገብሮ ስልጣን ላይ ከሚወጣ፥ የራስን ምኞትና አጅንዳ ገብሮ ኢትዮጵያን ማዳን አይሻልምን? ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
በዚህ ፅሁፍ ስለ አማራጭ ሃይሎች ትብብር አስፈላጊነት የታወቀ ነገር ስለሆነ መናገር አልፈልግም። ማተኮር የምፈልገው እንዴት ትብብሩ እንደሚመጣ መላ ፍለጋ ላይ ነው። ይህም ሲባል ነገሮች ተድበስብሰው አንድ ላይ ተጨፍልቀው ማየት ሳይሆን፥ በየደረጀው ከመነሻው እስከ መድረሻው ጥርት ባለ መልኩ ለማስቀመጥ ነው። ከውጭ ለሚያይ የብሔር ተኮር ሃይሎችና የኢትዮጵያ አንድነት ሃይሎች ተባብለው በሁለት ትልቅ ጎራ ተከፋፍለው በጥርጣሬ መተያየታቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው። ባብዛኛው ግን ልባቸው የሚፈልገው ለሁሉም አንድ ነው። ያም ሆኖ አንዳንድ ተስፋ ሰጭ ፍንጭ ከመታየቱ በቀር በሁለቱ ጎራ ዙሪያ ፈቀቅ ያለ ነገር እየተደረገ አይደለም። ስለዚህ አድበስብሰን ለመግባባት እስካሁን የሞከርነው ጠብ ስላላለ አዲስ መንገድ እንከተል። እስቲ ይህንን መንገድ በሶስት ደረጃ ከፍለን እንየው። 1ኛ/ ቅድመ መግባባት ለመሰባሰብ ነው 2ኛ/ መግባባት ለውይይት ነው 3ኛ/ ድህረ መግባባት ለአንድ ድምፅ ነው 1ኛ/ ቅድመ መግባባት ለመሰባሰብ ስለ ውይይት ከማውራታችን በፊት ከየጎራችን ወጥተን በአንድ ቤት ውስጥ መሰባሰብ ይኖርብናል። ስለዚህ ቅድመ መግባባት ከተለያየ ጎራችን አውጥቶን ወደ አንድ መካከለኛ ቤት እንድንሰበሰብ አቅም ይሰጠናል። ይህም ማለት ቅድመ መግባባት ዓላማው ሁሉንም አግባብቶ አንድ ላይ እንድንቀመጥ እንድንችል መፈቃቀድ እንዲኖረን የሚያደርግ ነው። ለያይተውን በየጎራችን ተዘልለን እንድንቀመጥ ከሚያደርጉን ነገሮች ይልቅ የምንስማማባቸው ነገሮች ይበልጣሉ። አፋችን የተለያየ ነገር ቢያወራም ልባችን የሚፈልገው ነገር ግን ይመሳሰላል። ይህ ቅድመ መግባባት እንዲኖር ልብ ለልብ መናበብ እንደ መጀመሪያ ስሌት መምረጥን ይጠይቃል። ከምናወራው ወሬ ይልቅ፥ ስሩ ጋ ሄደን አንዳችን የሌላውን ልብ ማዳመጥ ይኖርብናል። ልብ ለልብ ስንናበብ፥ ይህ ቅድመ መግባባት እውን ይሆንልናል። ለአብዛኛው ህዝብ ልብ ለልብ በመናበብ ቅድመ መግባባት ይፈጥራል ብዬ የማስበውን ከዚህ በታች እዘረዝራለሁ። ሀ/ መሬት ላይ ያለው ሕዝብ አንድ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔረሰብ ሳይለይ የተጨቆነና በድህነት ለዘመናት የኖረ ነው። በፍቅር ተጋብቶና ተዋልዶ ደጉንም ክፉውንም አብሮ የሚያሳልፍ ነው። በሕዝብ ደረጃ ጥልና መከፋፋት የለም። ለዳር ድንበሩ ብሔረሰብ ሳይለይ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ኢትዮጵያን እዚህ አድርሷታል። ኢትዮጵያ የተያያዘችው ተፈጥሯዊ (organic) በሆነው የፍቅር ሰንሰለትና አብሮነት ነው። ዛሬም ደምህ ደሜ ነው እያለ ፍቅሩን እየገለጠ የሚገኝ ወንድማማች ነው። ይህ የቅድመ መግባባት መሰረትና መነሻ ነው። ልሂቃንን የሕዝቡ ነፀብራቅ እንዲሆኑ ግድ የሚል እውነት ይህ ነው። ለ/ ልባችን ውስጥ ያለው ራዕይ አንድ ነው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ብለን ስናስብ የሚመጣልን ለሁሉ የምታጓጓውን ኢትዮጵያ ነው። ያም ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ሰፍኖባት፥ ሁሉም በእኩልነት፥ በነፃነት የሚኖርባት ሀገር የምትሆነው ናት። ሁላችንም ከሰፈነው መልካም አስተዳደር የተነሳ የሀገር ባለቤትነት ተሰምቶን ብሶታችንን ሳይሆን ኩራታችንን የምናውጅባት ሀገር የምትሆነው ናት። እኩልነትን መሰረት ባደረገው አንድነታችን ምክንያት ብልፅግና በፍትህ እንዲመጣልን ግድ የምትለን ሀገር የምትሆነው ናት። ይህ የቅድመ መግባባት ዓላማና ግብ ነው። በዚህ ራዕይ ቅድመ መግባባት ሁሉንም አግባብቶ ሁሉንም ያገባኛል ባይ መካከለኛ በሆነው የኢትዮጵያ ቤት አዳራሽ ውስጥ እንዲገኝ የግድ የለዋል። ሐ/ ድል የሚገኝበት የህብረት አካሄድ አንድ ነው። ተነጣጥለን እየተፎካከርን ብንገፋፋ ሁላችንም ባዶ እጅ መቅረታችን የታወቀ ነው። ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንዲሉ መደጋገፍና መተባበራችን ሃይላችን እንደሆነ ለሁሉም ግልፅ ነው። መከፋፈል ለመጥፋት ሲዳርገን፥ መያያዝ ደግሞ ለድል እንደሚያዘጋጀን እሙን ነው። ይህ ደግሞ የቅድመ መግባባት ስልት ነው። በዚህ ስልት አግባብቶ ሁሉንም ለድል እንዲሰለፉ ይችሉ ዘንድ አንድ ቦታ ለውይይት እንዲገናኙ አፅንዎት ይሰጣል። በነዚህ ከዚህ በላይ በተዘረዘሩት የጋሪዮሽ ነጥቦች ላይ መተማመንና መስማማት ካለ ቅድመ መግባባት አለ ማለት ነው። ቅድመ መግባባት ካለ ደግሞ በየጎራችን ተወስነን በስማ በለው ከመጯጯህ ይልቅ፥ ከየጎራችን ወጥተን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን ፊት ለፊት እየተያየን ለመወያየት ተዘጋጅተናል ማለት ነው። ስለዚህ ከቅድመ መግባባት በዋላ የሚመጣው ሁለተኛው ደረጃ ላይ የሚገኘው መግባባትን ደግሞ ቀጥለን እንይ። 2ኛ/ መግባባት ለውይይት በዚህ ክፍል ውይይት ለማድረግ ዝግጁ ነን ማለት ነው። አብረን ለመኖር ተስማማን እንጂ እንዴት እንኑር የሚለውን ለመፍታት ውስብስብና አስቸጋሪ ነገር ነው። ለኢትዮጵያ ያለን የመፍትኤ አመለካከት ልዩ ልዩ ነው። ግን በዚህ ልዩነት ላይ ፈርጀ ብዙ የሆነውን መፍትኤ ለመፈለግና ለመግባባት የብሔር ተኮር ሃይሎችና የኢትዮጵያ አንድነት ሃይሎች የሚባለው ጎራ ውስጥ መሰወር ትርጉም የለውም (በቅድመ መግባባት ያንን ፈተነዋልና)። ምክንያቱም በአስተሳሰብ ላይ ውይይት ሲደርግ ከኢትዮጵያይ አንድነት ሃይል ጎራ ነኝ የሚለው ሁሉ አንድ ዓይነት አመለካከት አይኖረውም። ከብሔር ተኮር ሃይሎች ጎራ ነኝ የሚለውም እንደዚሁ የተለያየ ዓይነት አስተሳሰብ ነው ያለው። በዚህ ስፍራ የብሔር ተኮር ሃይሎችና የኢትዮጵያ አንድነት ሃይሎች የሚለው መለያ አርማ፥ እየሆነ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከመግለፅ ይልቅ እውን ሊሆን የማይችለውን ቅራኔ በባዶ ሜዳ ያጋግላልና በቅድመ መግባባት መጀመሪያ ዕልባት ያግኝ የተባለው ለዚህ ነው። ይህ ሲባል በየብሔረሰቦች አይደራጁ ወይም በየብሔረሰብም አይወያዩ ማለት አይደለም። ግን የማታ ማታ የሚያያይዘን በጠረጵያ ዙሪያ ቁጭ ብለን እንድንወያይ የሚያደርገን በአንድ ቤት ውስጥ ለውይይት መቀመጥ ስንችል ነው። ቅድመ መግባባት ወደ አንድ ቤት ከሰበሰበን ዘንዳ ሰከን ብለን መወያየት እንችላለን ማለት ነው። በመፍትኤው ላይ ለመግባባት ቀጠሮ ሳንሰጠውና ለነገ ሳናሳድር ተወያይተን ዛሬ መንግስት በስራ ላይ ከሚተገብረው መፍትኤ ጋር በትይዩ አማራጭ የምንላቸውን አንድ፥ ሁለት፥ ሶስት ••• ብለን እንወስንና በነዚሁ ዙሪያ እንደ እምነታችን እንሰብሰብ። 3ኛ/ ድህረ መግባባት ለአንድ ድምፅ በመግባባት በተለያዩ አማራጭ መፍትኤዎች ዙሪያ ከተሰባሰብን የሚቀጥለው ድህረ መግባባት ነው። በድህረ መግባባት አማራጭ ሃይሎች ሁሉ የመፍትኤ ሀሳብ ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በመቀናጀት አንድ የጋራ የሆነ ድምፅ ይኖራቸዋል። ያም ድምፅ ለምሳሌ ዲሞክራሲና የመብት መከበር ጉዳይ ሊሆን ይችላል። በቅድመ መግባባትና በመግባባት ያሉትን ሁለት የቤት ስራዎች ሳንሰራ አማራጭ ሃይሎች አንድ ሁኑ ብሎ መጮህ የትም አላደረሰንም። ግን ጥርት አድርገን በየደረጃው ያሉትን ጥያቄዎች እየመለስን ብንሄድ የትብብር ስኬት የእኛ ነው። ማጠቃለያ ኢትዮጵያ ለማንም የመለያያ መለያ አርማ አትሆንም። ምክንያቱም የሁሉም ናትና። ስለዚህ እርስ በርስ ከመካሰስ፥ ከሁሉ በፊት ደረጃ በደረጃ ቅድመ መግባባቱ ተደርጎ፥ በልባችን የተግባባንባቸው ነጥቦች አቀራርበውን ሲያበቁ ያኔ እናስተውልና ድልድይ ሰርተን በአንድ ላይ ቁጭ ብለን ለመነጋገር እንሰብሰብ። እየተፈራራን ሩቅና ሩቅ ሆነን ከምንፈራረድ፥ በቀና መንፈስ ተቀራርበን ፈቀቅ የሚል ነገር እንወያይና በተወሰኑ የተለያዩ አማራጭ የመፍትኤ አሳቦች ላይ መግባባት ላይ እንድረስ። በመጨረሻም በድህረ መግባባት ተቀናጅተን በአንድ ድምፅ እንቁም። በዚህ መንገድ ብንቆርጥና ብንሄድ ለዓመታት እውን ያልሆነው ትብብር በወራት ውስጥ ብቅ ብቅ ማለት ይችላል ብዬ ተስፋ አደርጋለው። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ! ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
በኢትዮሚዲያ ላይ በለንደን ላይ ያደረጉትን ንግግር ከዚህ በታች የተቀነጨበውን አየውና ይህንን ልፅፍ ተነሳሳሁ። “የኦሮሞ ወጣቶችን ወክዬ ለውጭው ማህረሰብ የማስተላልፈው መልዕክት አለኝ። ካሁን በዋላ በኢትዮጵያ ቢሆን ቢሆን ታግለን መብታችንን አስመልሰን ከሌሎች ጋር አብረን እንኖራለን። ካልሆነ ግን ያችን ሀገር በታትነን ጥለናት እንሄዳለን እንጂ እንደ ትላንቱ የማይረቡት እላያችን ላይ ተጭነው እንዲያስተዳድሩን አንፈቅድም።” - ጀዋር መሐመድ፥ ከለንደን ንግግር ከኢትዮሚዲያ የተወሰደ። በመጀመሪያ አሳቤን ይረዱልኝ። በክርክር ለማሸነፍ አሳቡም ምኞቱም የለኝም። እርስዎንም እንደ ጠላት ለመቁጠርና ለመፈረጅ በልቤ ውስጥ ያለው ፍቅር አይፈቅድልኝም። ነገሬ ከአስተሳሰብዎ ጋር ነው። ለማሳመን ብዙ ትንታኔ አልገባም። ቃሌን አጭር በማድረግ ከቃሌ ጀርባ ያለውን ቅን መንፈስ እንዲረዱ ተስፋ ማድረግን እመርጣለሁ። እርስዎ እስላም እኔ ክርስቲያን፥ እርስዎ ኦሮሞ እኔ አማራ መሆናችን ለመግባባት እንቅፋት ይሆናል ብዬ አላስብም። ለእኔ እርስዎ የሀገር ልጅ ነዎት። ሃይማኖት የግል ሀገር የጋራ ነው የሚለውን አባባል ልቀያይረውና፥ በጥንድ እውነት መግለፅ ይፈቀድልኝ፤ ሃይማኖት የግል ፈጣሪ የጋራ ነው። ዘራችን የግል ኢትዮጵያ የጋራ ናት። ስለዚህም የጋራ በሆነ ነገር ላይ ሁለታችንም አንድ ነን። በዚህ መንፈስ እንዲያደምጡኝ አደራ እላለው። በመጀመሪያ ራሴን ላስተዋውቅና፥ እኔ ያለፈውን የታሪክ ቁርሾ በይቅርታ ዘግተን፥ የወደፊቱን ታሪካችንን በፍትህ መስርተን፥ ነፃ የሚያወጣንን እውነት ተነጋግረን፥ አዲሲቷን ኢትዮጵያ እንገንባ ብዬ የምሞግት ነኝ። ይህንን ካልኩ አሁን ወደ ዝርዝር ሀሳቤ ልግባ። የጎንደር ሕዝብ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ወንድምነት በአደባባይ አጋርነቱንና ፍቅሩን ሲያስተጋባ፥ የፍቅር ቋንቋ መናገሩን ያሳይ ነበር። ያንንም የፍቅር ጥሪ ወንድሙ የኦሮሞ ሕዝብ ተረድቶ፥ ምላሹን ፍቅሩንና አጋርነቱን በአደባባይ ሲያሳይ ፍቅርን መናገሩ እንደሆነ ይገልጥ ነበር። ይህንን የሕዝብ ፍቅር ቋንቋ ለምድራችን ፈውስ ተስፋ ጭላንጭል ያመጣል ተብሎ ሲጠበቅ፥ በዚህ ወሳኝ ወቅት በለንደን ያቀረቡት ንግግርዎ ተስፋውን በዜሮ እንዳባዙት ይቆጠራል። ይህንን ግልፅ ደብዳቤ ለመፃፍ የፈለኩት እንኪያ ሰላምታ ከእርስዎ ጋር ለመግጠም ሳይሆን፥ ለሚያየንና ለሚሰማን ሁሉ መግባባትን ፍንጥቅ ማድረግ ይቻል ይሆናል የሚል ተስፋ ፍቅር በልቤ ውስጥ ስለጫረብኝ ነው። ለዚህም የምተማመነው በሀገር ልጅነታችን ላይ ያለኝ አመኔታ ነው። ኢትዮጵያ የአንድነቷ መሰረት የሕዝቧ ማንነት ነው። የኢትዮጵያ አንድነት በመንግስት ስራ ወይንም መንግስት በሚያወጣው አዋጅ ቁጥጥር ስርም አይደለም። ነገሩን ካስተዋልነው በሊሂቃን አስተሳሰብና ፍልስፍና ስርም አይደለም። በእኔና በእርስዎ እጅም አይደለም። የታሪክ ጉዳይ ሆኖ የኢትዮጵያ አንድነት ጅማሬው ላይ የመንግስታት እጅ ቢኖርበትም፥ ሕዝቡን የሚያስተሳስረው ፍቅር ግን ሰው ሰራሽ አርተፊሻል ሳይሆን “ተፈጥሯዊነት”(organic) ነው። ይህን ሕዝቡ በታሪክ አጋጣሚና በፈጣሪ አሳብ አብሮ ለዘመናት በመኖር ያመጣው እውነታ ነው። ኦሮሞ ፍታዊ ሆኖ የሚኖርበት ለመድረስ በመንገዱ ላይ የቆመው ኢትዮጵያ ሳትሆን እንደ እርስዎ ያለው አስተሳሰብ ነው ብዬ እገምታለሁ። ለኔ ኢትዮጵያ ከኦሮሞ ተነጥሎ በኦሮሞ የድል መንገድ ላይ የቆመ ደንቃራ አድርጌ አልወስድም። ለምን ቢባል መላውን ኢትዮጵያ በጂኦግራፊ፥ በቤተሰብነት፥ በአብሮ ነዋሪነት፥ በደግነቱ አያይዞ፥ ተጋብቶ ተደባልቆና ተዋልዶ እዚህ ያደረሰው በተቀዳሚነት የኦሮሞ ሕዝብ ነው። ፍትህና ዲሞክራሲ ያለባት መድረሻ እንድትሆን የሚፈልጉት ኢትዮጵያ ከሆነ መነሻዎን ኢትዮጵያ ማድረግ ያለብዎት ይመስለኛል። ያልተነሱበትን ነገር መድረሻ ላይ አገኘዋለው ማለት ዘበት ነው። ለእኔ ኦሮሞ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩሕ ተስፋ ለመቅረፅ የመሪነቱን ሚና ይጫወታል። ለዚያም በሀገር ቤት ያለው የኦሮሞ ሕዝብ የመሪነቱን ሃላፊነት በብቃት እየተወጣው ነው። እርስዎስ አጥር ሆኖ ከሌላው ሕዝብ የሚከልልዎትን የውልጃ ማንነት ሳይለቁ(ወደው አይደለም ኦሮሞ ሆነው የተወለዱት)፥ በምርጫዎ ከሁሉ ሕዝብ ጋር በእኩልነት የሚያያይዝዎትን ኢትዮጵያዊነትን መርጠው በጋርዮሽ ቢሞግቱ ምን ይመስልዎታል? አንደኛ ኦሮሞ መሆንዎን መምረጥዎ ባልከፋ፥ መልካም ነውና። ለነገሩ ሁሉም በግሉ በመጀመሪያ የተለያየ ዘር ግኝት ነው። ታዲያ የሚያስተሳስረን ጉራጌው ጉራጌ ኢትዮጵያዊትን አንግቦ፥ ጋምቤላው ጋምቤላ ኢትዮጵያዊነትን ወዶ፥ ትግሬው ትግሬ ኢትዮጵያዊነትን መርጦ፥ አማራው አማራ ኢትዮጵያዊነትን ተቀብሎ ወዘተረፈ በጋሪዮሽ መያያዛችን ነው። ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ መሆንና ለኦሮሞ እኩልነት ማቀንቀን የሚቃረኑ አይደሉም፥ እንደውም የሚደጋገፉ እንጂ። ዋነኛው ጉዳይ ከኖርንም አብረን፥ ተበታትነን ከጠፋንም አብረን እንደሆነ በማወቅ የመቆራኘታችንን ሚስጢር ጥልቀቱን ማስተዋሉ ላይ ነው። ኢትዮጵያን በታትኖ ኦሮሞን መገንባት የሚለው አሳብ የማይሆን ነገር ነው። በኢትዮጵያ መቃብር ላይ የሚገነባ የኦሮሞ በረከት በዚያች ምድር ይኖራል ብሎ ማሰብ ከንቱ አስተሳሰብ ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መቃብር ካለ፥ ከኢትዮጵያ መቃብር ስር የኦሮሞ መቃብር አለ። ለምን ቢባል ከማንም ይልቅ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የሚያሰኛትና እንደ ደም ስር ሁሉንም የሚያያይዘው ኦሮሞ ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመዋለድና በመደባለቅ ስርና መሰረት ስለሆነ ነው። ነገር በምሳሌ እንዲሉ ሁላችንም ያለነው ውቂያኖስ ላይ የሚንሳፈፍ ኢትዮጵያ በሚባል ትልቅ መርከብ ላይ ነው። እርስዎ የሚሉት ቢሆን ቢሆን ተባብረን መርከቡን በእኩልነት እየኖርንበት እንሂድ፥ ካልሆነ መርከቡን በታትነን በኦሮሞ ጀልባ እንኖራለን ነው። ያስተውሉ፥ 1ኛ/ ሌላው ይበታተን የሚሉት ትልቁን 80 በላይ ብሔረሰብ የሚይዘውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ነው። 2ኛ/ ኦሮሞ እንደ ጀልባ በኢትዮጵያ መርከብ ላይ የተቀመጠ ማንነት ያለው አይደለም። ኦሮሞ የመርከቡ አካልና መካከለኛ ክፍል ነው። ይህ መሬት ላይ ያለ በሕዝቡ አብሮነት ለዘመናት የተገለጠ ሐቅ ነው። 3ኛ/ መርከቡ ከተበታተነ፥ የመርከቡ መካከለኛም አብሮ ሰምጦ ይቀራል። ከዚህ ውጭ ያለ አስተሳሰብ ሕልውና በሕልም ደረጃ ያለ ነው። 4ኛ/ የመርከቡን መሪ ማን ይያዝ የሚለው ጉዳይ የእኛ ምርጫ አይደለም። የእኛ ትግል መሪዉን ለመያዝ ሳይሆን፥ መሪዉን የሚይዘውን አካል ሕዝብ እንዲመርጥ እውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲኖር ነው። እውነተኛ ዲሞክራሲ ባለበት ብዙ የሕዝብ ቁጥር ያለው ኦሮሞ ከሁሉ ይበልጥ ይመቸዋል። ታዲያ የነገሬ ፍፃሜ ይህ ነው፥ ከ 50 ዓመታት በላይ ከቆየው የኦሮሞ ትግል ልምድ ከቀሰሙ በዋላ የደረሱበት ይህ አስተሳሰብዎ፥ ሁሉም የሚፈልገውን ይህንን ዲሞክራሲ እውን ለማድረግ የሚያስችል መላ በውኑ ነውን? ለማንኛውም ለሁላችንም ልቦና ይስጠን። አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ! ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
ሕዝብ ተነሳ። ይህ ከወትሮው የተለየ አነሳስ ይመስላል። ከአንዴም ሁለት ጊዜ ይህ ሕዝብ ተነስቶ ሲያበቃ እድሉን ለልጆቹ በአደራነት ሰጥቶ ሲቀመጥ፥ መሪዎቻችን የስልጣን ርክክብ አካሄደው ሕዝቡን በዜሮ እየሰደዱት ስልችቶታል። ቁጭ ብድግ ማለቱ በቃኝ ያለ ይመስላል። አሁን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መነሳቱ፥ የስልጣን ርክክብ ለማካሄድ ሳይሆን፥ ዳግም እንደገና መነሳት በማያስፈልገው ሁኔታ ስልጣኑን ራሱ ወስዶ ተረጋግቶ ለመቀመጥ ነው። ቀድሞ ነገር ባለጉዳዩ ሕዝብ ቁጭ ብሎ መሪዎቻችን ሲተራመሱና ሕዝቡን ራሱን ሲያተራምሱት ምንም ያለማድረጉ በውጭ ለተመልካች ሲታይ ምንም እንደማያውቅ ያስመስለው ይሆናል። እውነቱን ብንመረምር ግን የምናስተውለው ሁሉን አዋቂ እንደሆነና፥ ዝም ያሰኘው ትዕግስቱ መሆኑ በገባን ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲታገስ መሬት ነው። ይሸከማል፥ ይችላል። ረዥም ጊዜ ይሰጣል። ፅዋ ሲሞላና ጊዜው ሲደርስ ይህ ሕዝብ ጠያቂ ነው። በውጭ ሲታይ ሕዝቡ ጉዳይ ፈፅሙልኝ ብሎ አቤቱታ የሚያቀርብ ይመስላል። ግን አሁን እንደዚያ አይደለም። ቀረብ ብለን፥ አጥልቀን ብናይ ይህ ህዝብ በመልካም አስተዳድሩኝ እያለ መንግስትን እየተማፀነ አይደለም። ደግሞም ስም ጠርቶ እከሌ ይግዛኝ ብሎም እየተሟገተ አይደለም። ሕዝቡ እያለ ያለው ስልጣን የሕዝብ ነውና ለሕዝቡ የስልጣን ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥ ድምፁ እንዲሰማ ነው። መንግስት የሕዝብ ጥያቄ መልስ እሰጣለው ብሎ ጥልቅ ተሃድሶ ላካሂድ ብሎ ተነስቷል። ተቃዋሚ የሕዝብ ጥያቄ እመልሳለው ብሎ ሕገ መንግስት ለማርቀቅ ተነስቷል። በፊት ለፊት የማይታየውን እውነት ለማየት ብንጥር ግን ሕዝብ እያለ ያለው፥ ጊዜው የሁለቱም ተፎካካሪዎች የመምራት ጉዳይ ሳይሆን ሕዝቡ ራሱ የሚመራበት ወቅት መሆኑ ነው። ጊዜው መሪዎቻችን ስፍራቸውን ለሕዝቡ ምሪት የሚለቁበት እንጂ በየፊናቸው በነፍስ ወከፍ ለመምራት ሽር ጉድ የሚሉበት ጊዜ አይደለም። ይልቁንስ ሕዝብ መሪዎቹን ለመምረጥ የስልጣን ባለቤት ሆኖ፥ ድምፁ የሚሰማበትና የሚከበርበትን መድረክ ለማመቻቸት እንወያይና እንግባባ። መንግስትም ሰምቶ ይታዘዝ፥ ተቃዋሚም ሰምቶ ይቀናጅ። የሕዝቡ ቆራጥነት የትዕግስቱ ውጤት ነው። ጊዜው እስኪደርስ ትዕግስቱ ሲገርም፥ ጊዜው ሲደርስ ደግሞ ቁርጠኝነቱ የሚደንቅ ነው። ውሎ እንዲያድር ፋታ አይሰጥም። በውጭ ሲታይ ለብዙ ጊዜ የታየው ትዕግስቱ አሁንም አለ ብለን እንታለል ይሆናል። ሕዝቡ ከዝምታውና ከመቀመጫው ሲነሳ ቶሎ ብሎ መታዘዝ ማስተዋል ነው። የለመደች ጦጣ ሁልጊዜ ሽምጠጣ ብለን እንደለመድነው እንቀጥል ብንል፥ መሬት የሆነው ሕዝብ እሳት ሆኖ ይበላናል። ስልጣኑን የያዘው የሙጥኝ ማለቱን ትቶ፥ ተቃዋሚዉም ስልጣኑን መቋመጡን ትቶ፥ ሕዝቡ ልምራ ሲል በእሽታ ሁሉም የየግል ምኞቱን ለቆ ይመራ። ለዚህም ዓላማ ይህ ሕዝብ በእውነት የስልጣኑ እውነተኛ ባለቤት የሚሆንበትን መፍትኤ በአስቸኳይ ይመከርበት። አሁን ልተርክ የተነሳሁት ፊት ለፊት ያለውንና ሁላችንም ያሰለቸንን፥ ግን እውነት ስለሆነው ታሪካችንና ተጨባጭ ሁኔታዎቻችን አይደለም። ደግሞም እውነቱ አድክሞኝ የሌለ ነገር ፈጥሬ አፈታሪክ ለማውራትም አይደለም። ዓላማዬ ፊት ለፊት ከሚታየው እውነት ጀርባ ያለውን ግዙፉን የማይታየውን እውነት አስተውለን፥ የሚገርመውን ነገር እንድናውቅ ነው። እንዴት ማለት ጥሩ ነው። እንግዲህ ከስር መሰረቱ እንጀምር። 1ኛ/ ሕዝቡ የሚገርም ነው። የሕዝቡ ማንነት የሚገርም ነው። በመሪዎቻችን ማንነት ሕዝቡ ማንነቱን ተጠልፎ መነጋገሪያ የሆነው የመሪዎቻችን ማንነት ነው። ማን ያውራ ስለ ደጉ ሕዝብ? ማን ያውራ በፍቅር ስለሚተሳሰበው ሕዝብ። ሲራብ አብልቶ፥ ሲጠማ አጠጥቶ፥ አብሮ ተቻችሎና ተጋብቶ ለዘመናት የሚኖረውና የሚያኖረው ሕዝብ ማን ማንነቱን ያራግብለት? ያደከመን በመሪዎቻችን ማንነት ላይ የተመሰረተ የፊት ለፊት እውነት እያወራን ስጋታችን መብዛቱ ነው። ሁሉም ዓላማውን የሚያራምደው ኢትዮጵያን የመሪዎቻችን ነፀብራቅ አድርጎ በመውሰድ ነው። ከላይ ላይ ከሚታየው እውነት ጀርባ የተደበቀውና በጊዜ ተፈትኖ ያለፈው ትልቁ ጥልቅ እውነት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቤተሰብነት ነው። 2ኛ/ የሀገር ልጅ የሚገርም ነው። መሪዎቻችን ሁሉ ሲታዩ ለየቅል ናቸው፦ ኢአዴግ፥ ግንቦት ሰባት፥ መድረክ፥ ሰማያዊ፥ ኦነግ፥ ወዘተረፈ። እንደገና ግልፅ ከሆነውና ከምናውቀው እውነት ጀርባ ያለውን የማይታየውን እውነት ለማየት ብንጥር ሁሉም የሀገር ልጆች ናቸው። ይህም በራሱ ክብር ነው፥ ምክንያቱም ከታላቁ ሕዝብ አብራክ የወጡ የሕዝቡ ልጆች ስለሆኑ ነው። የሀገር ልጆች ስለሆኑም በውስጣቸው ያለው እስከ ዛሬ ያልታየው ችሎታቸው ታሪክ ለመስራት አቅም አለው። እነዚህ የሀገር ልጆች ድንቅ የሆነው ችሎታቸውና እምቅ አቅማቸው እስካልተገለጠ ድረስ አንዱ ሌላኛውን ለማጥፋት መሮጣቸውን አያቆሙም። ይህ ያልተገለጠው አቅም በውስጥ የሀገር ልጅነት እውን እንደሆነ ሁሉ በገሀዱ ዓለም እውን ሆኖ እንዲወጣ ተአምር ይጠይቃል። ተአምር ማለት ሲደረግ ታይቶ የማይታወቅና፥ ይሆናልም ተብሎ ሊታሰብ የማይችል ነገር ሲሆን ነው። 3ኛ/ ውይይትና መግባባት የሚገርም ነው። በሀገር ልጆች ያለው እምቅ አቅም የሚገለጠው፥ በሕዝቡ ቆራጥ ግፊት መሪዎቻችን ውይይትና መግባባትን የችግራችን መፍቻ አድርገው መጠቀም ሲችሉ ነው። ይህ ተአምር የአገር ልጆችን እርስ በርሳቸው ተጨፍልቀው አንድ ወጥ እንዲሆኑ የሚያደርግ ሳይሆን፥ እያንዳንዳቸው ውይይትና መግባባትን ተክነውበት፥ ስልጣኑን ባለቤት ለሆነው ሕዝብ ማስረከብ የሚችሉበት መድረክ የሚፈጥር ነው። ተአምሩ ዲሞክራሲና እኩልነት አይደለም። እነዚህ እሴቶች ተአምራት ከሆነው ውይይትና መግባባት የሚገኙ ውጤቶች ናቸው። ይህም እንደ ድሮ በጠጉረ ልውጥ አሳላፊነት የሚካሄድ ሳይሆን በሀገር ልጆች ሽማግሌነት እውነትን ብቻ ዋና መሰረት አድርገው የሚተገብሩት ጉዳይ ነው። ፊት ለፊት ያለውን የውጭውን ብቻ ለሚያይ ሰው፥ ውይይትና መግባባት መንግስትን በስልጣን የሚያስቀጥል ጊዜ መግዣ እኩይ ተግባር፥ ወይም ተቃዋሚን በአቋራጭ ስልጣን ላይ የሚያስቀምጥ መሰሪ ድርጊት አድርጎ ይወስዳል። የማይታየውን እውነታ ጠጋ ብሎ ለማየት የታደለ ግን፥ ውይይትና መግባባት እስከ ዛሬ ያልተፈተነ ተግባር ሆኖ፥ የሀገር ልጅነትን ውበት ከመሪዎቻችን ውስጥ አውጥቶ እንደ ብሩህ ብርሃን የሚያስፈነጥቅና፥ ለሕዝብ የስልጣን በላይነት ተገዥዎች እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው። 4ኛ/ የሚጠበቀው ነገር የሚገርም ነው። ከእንግዲህ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የለም። ማንም ላይታመን፥ ሕዝቡ ራሱን ብቻ ሊያምን ተነስቷል። ስልጣን የሕዝብ ነው እያሉ በስሙ የሚነግዱ ከእንግዲህ በቃችሁ ተብለዋል። ስልጣን የሕዝብ መሆኑን የሚናገር ሳይሆን በሕዝቡ ለመመራት ራሱን የሕዝቡ ተከታይ የሚያደርግ ብቻ ይፈለጋል። ከትልቅ ትዕግስት በዋላ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሕዝቡ የተነሳው፥ ለመንግስት ስልጣኑን የሚያስረዝምበትን መላ ለማፈላለግ፥ ወይም ለተቃዋሚ የስልጣን ውርስ እንዲያደርጉ ለማመቻቸት ሳይሆን፤ መሪዎቻችን የሕዝቡን ድምፅ እንዲሰሙ እና ስልጣንን ለባለቤቱ (ሕዝብ) ማስረከቢያውን መንገድ እንዲፈጥሩ ነው። ፈሪሃ ፈጣሪ ያለው ይህ ሕዝብ አምላክ እንዳለለት ይታወቅለት። ኢሜል አድራሻ፦ ethioFamily@outlook.com ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
|
Details
MemberZelalem Eshete, Ph.D.
Deeper Walk With God Book on Ethiopia
This book makes a case for a paradigm shift in our thinking on the matter of Ethiopia. Instead of feeling powerless in our usual political saga, ethnic divide, and religious tensions, the book motivates us to look deeper, rediscover our true identity, and arise to make change. The greater power of change is with the people. The world has heard enough of our suffering. Let's spotlight the other face of Ethiopia: To Be Known As We Truly Are.
The world has heard enough of our lack of civilization. Let's spotlight the other face of Ethiopia: We Are One Big Intelligent Family. The world has heard enough of our poverty. Let's spotlight the other face of Ethiopia: Going Global Together. |